በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመዓት ቀን መጽሐፍ—በዓይነቱ ልዩ የሆነ የጥናት ውጤት

የመዓት ቀን መጽሐፍ—በዓይነቱ ልዩ የሆነ የጥናት ውጤት

የመዓት ቀን መጽሐፍ—በዓይነቱ ልዩ የሆነ የጥናት ውጤት

የፈረንሳይ ግዛት የሆነችው የኖርማንዲ መስፍን የነበረው ዊሊያም በ1066 ዓ.ም. እንግሊዝን ድል አድርጎ ያዘ። ከአሥራ ዘጠኝ ዓመታት በኋላ ዊልያም በአዲሱ ግዛቱ ላይ ጥናት እንዲካሄድ ትእዛዝ ሰጠ። ይህ የጥናት ውጤት ጥንቅር ‘የመዓት ቀን መጽሐፍ’ ተብሎ ተሰየመ። ለመሆኑ ይህ መጽሐፍ እንግሊዝ ውስጥ አሁንም ድረስ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው የታሪክ መዛግብት አንዱ የሆነው ለምንድን ነው?

ዊሊያም መስከረም 1066 ላይ እንግሊዝ ውስጥ ባለችው ሄስቲንግስ ከተማ አቅራቢያ ሰፈረ። ዊልያም በዚህ አካባቢ ባደረገው ጦርነት የእንግሊዝ ንጉሥ የሆነውን የሀሮልድን ሠራዊት ጥቅምት 14 ላይ ድል ያደረገ ሲሆን ንጉሡም ተገደለ። በኋላ ላይ ድል አድራጊው በመባል የታወቀው ዊሊያም ታኅሣሥ 25, 1066 በለንደን ከተማ በሚገኘው በዌስትሚኒስተር ቤተ ክርስቲያን ዘውድ ጫነ። ታዲያ እንግሊዛውያን በአዲሱ ንጉሣቸው አገዛዝ ምን ይገጥማቸው ይሆን?

ታላቁ የጥናት ውጤት

ንጉሥ ዊሊያም ቀዳማዊ የአገሪቱን ሰሜናዊ ክፍል ሙሉ በሙሉ ያወደመ ከመሆኑም በላይ አካባቢውን ሰው አልባ በማድረግ ሰፋፊ ቦታዎችን ያዘ። የቀድሞው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩት ትሬቨር ሮውሌይ ሁኔታውን አስመልክተው ሲጽፉ “በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ላይ በተደጋጋሚ የደረሰው ከባድ ጥቃት (ከ1068-70) በዘመኑ በነበረው በጣም ኋላቀር የሆነ መሥፈርት እንኳ ቢለካ አረመኔያዊ ነው ተብሎ መፈረጅ አለበት” ብለዋል። ዊሊያም የማያባራ ሕዝባዊ ዓመፅ ይነሳበት የነበረ ሲሆን ቁጥሩ ወደ አሥር ሺህ ገደማ የሚሆነው ወራሪ ሠራዊቱ የሚኖረው ለእሱ ጥላቻ ባለው ሁለት ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ መካከል ነበር። ውሎ አድሮ የኖርማንዲ ሕዝቦች በመላው አገሪቱ ከ500 በላይ የሚሆኑ መከላከያ ግንቦችን የሠሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በጣም ዝነኛው ታወር ኦቭ ለንደን (የለንደኑ ግንብ) በመባል የሚታወቀው ነው።

ዊሊያም እንግሊዝን በወረራ ከያዘ ከ19 ዓመታት በኋላ ይኸውም ታኅሣሥ 1085 ከለንደንና ከዊንቼስተር በስተቀር በመላ አገሪቱ ጥናት ማካሄድ ስለሚቻልበት መንገድ እቅድ ለመንደፍ ከባለሥልጣናቱ ጋር ለአምስት ቀናት በግላስተር፣ እንግሊዝ ውስጥ ስብሰባ አድርጎ ነበር። በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ላይ የንጉሡ መልእክተኞች የየግዛቶቹን አስተዳዳሪዎች ለመጠየቅና የአገሪቱን ሀብት ለመገምገም ወደ ሰባት ግዛቶች በተመሳሳይ ጊዜ ተላኩ።

ንጉሡ ለሠራዊቱ የሚከፍለው ገንዘብ ማግኘት አስፈልጎት ነበር። በተጨማሪም ከመሬት ባለቤትነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ውዝግቦችን መፍታት ነበረበት። እነዚህ ችግሮች እልባት ማግኘታቸው ከኖርማንዲና ከሌሎች የፈረንሳይ አካባቢዎች የመጡ ሕዝቦች በእንግሊዝ መስፈር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ የኖርማኖች የበላይነት እንዲቀጥል ያደርግ ነበር።

“የመዓት ቀን”

ንጉሥ ዊሊያም እንግሊዝን ድል ካደረገ ብዙም ሳይቆይ በእንግሊዛውያን ባላባቶች ሥር የነበረውን መሬት ቀምቶ ለኖርማን መኳንንት ሰጥቷቸው ነበር። በእንግሊዝ ላይ ያካሄደው ጥናት እንዳሳየው ከሆነ በወቅቱ በመላው አገሪቱ ከሚገኘው ሀብት ግማሽ የሚሆነው 200 በማይሞሉ ሰዎች እጅ ይገኝ የነበረ ሲሆን ከእነዚህ መካከል እንግሊዛውያን የሆኑት ሁለት ብቻ ነበሩ። ወደ 6,000 ገደማ ከሚሆኑት እንግሊዛውያን የመሬት ተከራዮች መካከል አብዛኞቹ ከ1066 ዓ.ም. በፊት የራሳቸው ይዞታ በነበረው መሬት ለመጠቀም ኪራይ ከመክፈል ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም፤ ድሆችና መሬታቸውን የተነጠቁት ደግሞ ሕይወታቸውን ለማቆየት ይፍጨረጨሩ ነበር።

ጥናቱ ኖርማኖች ከእንግሊዛውያን ለወሰዱት መሬት የባለቤትነት መብት እንዲያገኙ ሕጋዊ ፈቃድ ሰጠ። በተጨማሪም ጥናቱ፣ ግብር ለመሰብሰብ ያመች ዘንድ በደን የተሸፈኑና ሜዳማ የሆኑ ቦታዎችን ጨምሮ ለመሬትና ለኪራይ ቤቶች አዲስ የዋጋ ግምት እንዲወጣ አደረገ። እንደ በሬ፣ ላምና አሳማ ያሉ እንስሳት እንኳ ሳይቀሩ በነፍስ ወከፍ በጥናቱ ውስጥ ተካተው ነበር። በጭቆና ሥር ያሉት እንግሊዛውያን፣ የተካሄደውን ጥናት አስመልክቶ ለማንም አቤት ማለት እንደማይቻል ስለሚያውቁ የጥናት ውጤቱ ሥጋት ፈጥሮባቸው ነበር። በመሆኑም ይህን ታላቅ የጥናት ውጤት “ከፍርድ ቀን” ወይም “ከመዓት ቀን” ጋር አመሳሰሉት። የጥናት ውጤቱ ከጊዜ በኋላ ‘የመዓት ቀን መጽሐፍ’ የተባለውም በዚህ የተነሳ ነው።

የመዓት ቀን መጽሐፍ በብራና ላይ በላቲን ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን የተዘጋጀውም በሁለት ጥራዞች ነው። ሰፋፊ በሆኑ ወረቀቶች ላይ የተጻፈው ትልቁ የመዓት ቀን መጽሐፍ 413 ቅጠሎች ያሉት ሲሆን ትንሹ የመዓት ቀን መጽሐፍ ደግሞ አነስተኛ መጠን ባላቸው 475 ቅጠሎች ላይ የተጻፈ ነው። * ይህ መጽሐፍ ዊሊያም በ1087 ዓ.ም. በሞተ ጊዜ ገና ተጽፎ አልተጠናቀቀም ነበር። ይህ ሁሉ በአንድ ዓመት ውስጥ ሊከናወን የቻለው እንዴት ነበር?

ኖርማኖች፣ ባለርስቶችንና ጪሰኞችን የሚመለከቱ መረጃዎችን አልፎ ተርፎም ከገንዘብ አያያዝና ከግብር አሰባሰብ ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ጨምሮ እንግሊዛውያን ሲጠቀሙበት የነበረውን መንግሥታዊ አሠራር ወርሰው ነበር። ከዚያም ኖርማኖች ይህን አሠራር እንደ መሠረት አድርገው በመጠቀም አዲስ የግብር ተመን አዘጋጁ፤ ለዚህም ሲባል ሹማምንትን ወደ እያንዳንዱ ግዛት በመላክ ከሕዝቡ መረጃ አሰባሰቡ።

መጽሐፉ በዛሬው ጊዜ

በመካከለኛው ዘመን ላይ ‘የመዓት ቀን መጽሐፍ’ ከንጉሣውያን ቤተሰብ እጅ አይወጣም ነበር። መጽሐፉ መጀመሪያ ላይ በዋነኝነት የሚያገለግለው የመሬት ይገባኛል ውዝግቦችን ለመፍታት ነበር፤ ይሁን እንጂ በ18ኛው መቶ ዘመን እውቅ የሕግ ባለሙያ የሆኑት እንግሊዛዊው ሰር ዊሊያም ብላክስቶን ከጪሰኞች መካከል ድምፅ የመስጠት መብት ያላቸው እነማን እንደሆኑ ለማወቅ መጽሐፉን ይጠቀሙበት ነበር። መጽሐፉ በተለያዩ ስፍራዎች ይቀመጥ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን የሚገኘው በዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ ቤተ መዛግብት ውስጥ ነው።

በ1986 የመጽሐፉን 900ኛ ዓመት ለመዘከር ሲባል አምስት ቦታ ተከፋፍሎ በድጋሚ ተጠረዘ። ምሑራንና ታሪክ ጸሐፊዎች ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ የተተረጎመውንና ተሻሽሎ የተዘጋጀውን የዚህን መጽሐፍ ቅጂ ማግኘት ይችላሉ። አንድ የቢቢሲ ዘጋቢ ስለ መጽሐፉ እንዲህ በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል፦ “ለብሔራዊ ቤተ መዛግብት መሠረት የሆነ መዝገብ ነው፤ እንዲሁም ዛሬም ድረስ ለመሬት ባለቤትነት እንደ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ተቀባይነት ያለው ሕጋዊ ሰነድ ነው።” በ1958 በአንድ ጥንታዊ ከተማ ውስጥ የሚገኝ አንድ የገበያ ስፍራ፣ ባለበት የመቀጠል መብት ይኖረው እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ይህ መጽሐፍ እንደ ማስረጃ ሆኖ አገልግሎ ነበር።

የአርኪዎሎጂ ባለሙያዎች በመካከለኛው ዘመን ላይ እንግሊዛውያንና ኖርማኖች ሰፍረውባቸው የነበሩ ቦታዎችን ለማወቅ ዛሬም ድረስ የመዓት ቀን መጽሐፍን ይጠቀማሉ። ይህ መጽሐፍ ለእንግሊዝ ሕዝብ እድገት መሠረት የጣለ በዓይነቱ ልዩ የሆነ እጅግ አስፈላጊ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ማገልገሉን ቀጥሏል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ታላቁ የመዓት ቀን መጽሐፍ ግብር የሚከፈልባቸውን ንብረቶች ዝርዝር አጠር ባለ መልኩ ይዟል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ትንሹ የመዓት ቀን መጽሐፍ ሰፋ ባለ መንገድ የተዘጋጁ ዝርዝሮችን የያዘ ሲሆን በትልቁ ጥራዝ ላይ ያልተካተቱ መረጃዎችን ይዟል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የዊሊያም የመስቀል ጦርነት

ዊሊያም፣ ያካሄደውን ወረራ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የመስቀል ጦርነት እንደሆነ አድርገው እንዲያውጁለት ሐሳብ ያቀረበ ሲሆን በምላሹም ችግር የሚፈጥረው የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ ለእሳቸው ሥልጣን እንዲገዛላቸው የሚያደርግ መሆኑን ቃል ገባላቸው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ያለምንም ማቅማማት በሐሳቡ ተስማሙ። ይህም ለዊልያም “ዲፕሎማሲያዊ ድል” እንደነበረ ፕሮፌሰር ዴቪድ ሲ ዳግላስ ጽፈዋል። ሌላው የታወቁ ታሪክ ጸሐፊ ጆርጅ ኤም ትሬቬሊያን ደግሞ ሂስትሪ ኦቭ ኢንግላንድ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የዊሊያምን ሐሳብ መደገፋቸውና ቡራኬ መስጠታቸው በጦር ኃይል ተጠቅሞ ዝርፊያ እንደመፈጸም ተደርጎ ሊታይ ይችል የነበረውን አድራጎቱን እንደ ቅዱስ ጦርነት ተደርጎ እንዲታይለት ጠቅሞታል” በማለት ሐሳባቸውን አጠቃለዋል።

[የሥዕሉ ምንጭ]

© The Bridgeman Art Library

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

እንግሊዝ

ለንደን

ሄስቲንግስ

የእንግሊዝ ቻነል

ኖርማንዲ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]

Book: Mary Evans/The National Archives, London, England