በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጉርምስና ዕድሜ​—ሙሉ ሰው ለመሆን ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት

የጉርምስና ዕድሜ​—ሙሉ ሰው ለመሆን ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት

የጉርምስና ዕድሜ​—ሙሉ ሰው ለመሆን ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት

በጣም ሞቃት ከሆነ ደሴት ተነስተህ ቀዝቃዛ ወደሆነ አካባቢ ሄድክ እንበል። ልክ ከአውሮፕላን ስትወርድ አጥንት የሚሰብር ቀዝቃዛ አየር ተቀበለህ። ከዚህ የአየር ጠባይ ጋር መላመድ ትችል ይሆን? አዎ ትችላለህ፤ ሆኖም አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ይኖርብሃል።

ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ወደ ጉርምስና ዕድሜ በሚሸጋገሩበት ጊዜ የሚያጋጥማችሁ ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ልክ እንደ አየሩ ሁኔታ የልጆቻችሁም ባሕርይ በአንድ ጀንበር እንደተለወጠ ይሰማችሁ ይሆናል። በአንድ ወቅት ከሥራችሁ የማይጠፋው ልጅ አሁን ከእናንተ ይልቅ ከእኩዮቹ ጋር መሆንን ይመርጣል። እንዲሁም ውሎዋን አንድም ሳታስቀር ዝክዝክ አድርጋ ትናገር የነበረችው ልጃችሁ አሁን አጫጭር መልሶችን ከመስጠት አታልፍም። ለምሳሌ ያህል፦

“ዛሬ ትምህርት እንዴት ነበር?” ብላችሁ ስትጠይቋት

“ደኅና ነው” ብላ በአጭሩ ትመልስላችኋለች።

ዝምታ ይሰፍናል።

“ምን እያሰብሽ ነው?” ብላችሁ ስትጠይቋት ደግሞ

“ምንም” ትላችኋለች።

አሁንም ዝምታ ይሰፍናል።

ልጆቹ ምን ሆነዋል? ሚስጥሩን መፍታት (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “ከመድረክ በስተጀርባ ያለውን የልጆቻችሁን ሕይወት ለማየት የይለፍ ፈቃድ ያላችሁ ያህል” ሆኖ ይሰማችሁ የነበረበት ጊዜ ብዙ ሩቅ አልነበረም። “አሁን ግን ያላችሁ አማራጭ ከሌሎች ተመልካቾች ጋር ቁጭ ብላችሁ [የልጆቻችሁን ሕይወት] ማየት ብቻ ነው፤ ያውም የምታገኙት ቦታ ጥሩ ላይሆን ይችላል።”

ታዲያ በልጆቻችሁ ሕይወት ውስጥ የሚከናወነውን ነገር ከሩቅ ከመመልከት አልፋችሁ ከእነሱ ጋር መቀራረብ አትችሉም ማለት ነው? በፍጹም። ልጆቻችሁ በጉርምስና ዕድሜ ውስጥ በሚያልፉበት ጊዜም ከእነሱ ጋር ያላችሁ ቅርበት እንደ ድሮው እንዲቀጥል ማድረግ ትችላላችሁ። በመጀመሪያ ግን በዚህ አስደናቂ ሆኖም አስቸጋሪ የዕድሜ ክልል ውስጥ ስለሚከናወኑት ነገሮች መረዳት ያስፈልጋችኋል።

ከልጅነት ወደ አዋቂነት መሸጋገር

ተመራማሪዎች አንድ ልጅ አምስት ዓመት ሲሞላው አንጎሉ ሙሉ ሊባል የሚችል የእድገት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ያስቡ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ከዚህ ዕድሜ በኋላ በአንጎሉ መጠን ላይ ብዙም ለውጥ ባይታይም አንጎሉ የሚያከናውናቸውን ነገሮች በተመለከተ ይህን ማለት እንደማይቻል አምነዋል። ልጆች ጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚደርሱበት ጊዜ በሚያስቡበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር የሆርሞን ለውጥ በሰውነታቸው ውስጥ መከናወን ይጀምራል። ለምሳሌ ትናንሽ ልጆች በግልጽ የተቀመጡትን ካልሆነ በስተቀር ነገሮችን አዙረው አይመለከቱም፤ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ግን ከአንድ ጉዳይ በስተጀርባ ያለውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ነገሮችን ለማመዛዘን ይጥራሉ። (1 ቆሮንቶስ 13:11) የራሳቸው የሆነ አቋም መያዝ የሚጀምሩ ሲሆን ይህንንም ከመግለጽ ወደኋላ አይሉም።

በጣሊያን የሚኖረው ፓኦሎ በጉርምስና ዕድሜ በሚገኘው ልጁ ላይ እንዲህ ዓይነት ለውጥ አስተውሏል። እንዲህ ብሏል፦ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ልጄ እንደ ትልቅ ሰው እየሆነብኝ ነው። እንዲህ እንድል ያደረገኝ አካላዊ እድገቱ ብቻ አይደለም። ከዚህ ይበልጥ የሚያስደንቀኝ የሚያስብበት መንገድ ነው። አመለካከቱን ከመግለጽም ሆነ ትክክል መሆኑን ለማሳመን ጥረት ከማድረግ ወደኋላ አይልም!”

እናንተስ በጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚገኘው ልጃችሁ ላይ እንዲህ ዓይነት ለውጥ አስተውላችኋል? ምናልባት በልጅነቱ የታዘዘውን ሳያንገራግር ያደርግ ይሆናል። ልጁ ‘ለምን?’ የሚል ጥያቄ ቢያነሳ እንኳ “ስላዘዝኩህ ነዋ!” የሚል መልስ ከተሰጠው የተባለውን ያደርግ ነበር። በጉርምስና ዕድሜ ላይ ሲሆን ግን አንድ ነገር የሚደረግበትን ምክንያት ማወቅ ይፈልጋል፤ እንዲያውም ቤተሰቡ የሚመራባቸው ደንቦች ትክክል ስለመሆናቸው ጥያቄ ማንሳት ሊጀምር ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ልጁ አመለካከቱን በግልጽ መናገሩ እንደ ዓመፀኛ ያስቆጥረው ይሆናል።

ይሁን እንጂ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ የምትመሩባቸውን ደንቦች ለመቀየር እንደተነሳ አድርጋችሁ አታስቡ። ምናልባት የምትመሩባቸውን ደንቦች ለመቀበል ማለትም ሕይወቱን በእነዚህ ደንቦች ለመምራት ከራሱ ጋር እየታገለ ሊሆን ይችላል። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ቤት እየቀየራችሁ ነው እንበል። ዕቃዎቻችሁን ስታጓጉዙ አዲሱ ቤታችሁ ውስጥ ለሁሉም ዕቃዎቻችሁ የሚሆን ቦታ ማግኘት ቀላል ይሆናል? ላይሆን ይችላል። ይሁንና ውድ እንደሆነ አድርጋችሁ የምትመለከቱትን ዕቃ ቦታ ስላላገኛችሁለት ብቻ አውጥታችሁ እንደማትጥሉት የታወቀ ነው።

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁም “ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ” ለሚኖርበት ጊዜ ራሱን ሲያዘጋጅ ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጥመዋል። (ዘፍጥረት 2:24) እርግጥ ነው፣ ልጃችሁ ገና አዋቂ ስላልሆነ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ይቀረዋል። ሆኖም አዋቂ ሲሆን የሚጠቀምባቸውን ዕቃዎች ከወዲሁ እየሰበሰበ ነው ሊባል ይችላል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ፣ ወላጆቹ ያስተማሩትን መሥፈርቶች የሚመረምር ሲሆን ከእነዚህ መካከል አዋቂ ሲሆን የሚጠቀምባቸው የትኞቹ እንደሆኑ ይወስናል። *

ልጃችሁ እንደነዚህ ያሉትን ውሳኔዎች እንደሚያደርግ ማሰቡ በራሱ ያስፈራችሁ ይሆናል። ያም ሆኖ ልጃችሁ ትልቅ ሰው በሚሆንበት ጊዜ፣ ካስተማራችሁት መሥፈርቶች መካከል ሕይወቱን የሚመራው እሱ ከፍ አድርጎ በሚመለከታቸው መሥፈርቶች ብቻ እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ። በመሆኑም በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያለው ልጃችሁ ወደፊት የሚመራባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥልቀት መመርመር የሚኖርበት አሁን ከእናንተ ጋር እያለ ነው።​—የሐዋርያት ሥራ 17:11

በእርግጥም በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ይህን ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው። ደግሞም ዛሬ የእናንተን መሥፈርቶች ያላንዳች ጥያቄ የሚቀበል ከሆነ ነገ የሌሎች ሰዎችን መሥፈርቶችም በጭፍን ሊቀበል ይችላል። (ዘፀአት 23:2) እንዲህ ያለው ወጣት በሌሎች ተጽዕኖ በቀላሉ የሚሸነፍ በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ማስተዋል የጐደለው” ተብሎ ተገልጿል። (ምሳሌ 7:7) የራሱ አቋም የሌለው ወጣት ‘በማዕበል የሚነዳ ይመስል በማንኛውም የትምህርት ነፋስና በሰዎች የማታለያ ዘዴ የሚንገዋለል እንዲሁም ወዲያና ወዲህ የሚል’ ይሆናል።​—ኤፌሶን 4:14

ልጃችሁ እንዲህ ያለ ሰው እንዳይሆን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ከዚህ በታች የቀረቡት ሦስት እሴቶች እንዲኖሩት ጥረት አድርጉ።

1 የማስተዋል ችሎታ

ሐዋርያው ጳውሎስ “ጎልማሳ ሰዎች” “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት [እንደሚያሠለጥኑ]” ጽፏል። (ዕብራውያን 5:14) ምናልባት ‘እኔ እኮ ትክክል ወይም ስህተት ስለሆነው ነገር ለልጄ ያስተማርኩት ከዓመታት በፊት ነው’ ልትሉ ትችላላችሁ። ይህ ሥልጠና በጊዜው እንደጠቀመውና አሁን ላለበት የእድገት ደረጃ እንዳዘጋጀው ጥርጥር የለውም። (2 ጢሞቴዎስ 3:14) ያም ቢሆን ጳውሎስ ሰዎች የማስተዋል ችሎታቸውን ማሠልጠን እንደሚያስፈልጋቸው ተናግሯል። ትናንሽ ልጆች ትክክል ወይም ስህተት ስለሆነው ነገር እውቀት ሊኖራቸው ይችላል፤ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ግን ‘በማስተዋል ችሎታቸው የጎለመሱ’ መሆን ያስፈልጋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 14:20፤ ምሳሌ 1:4፤ 2:11) በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ በማመዛዘን ችሎታ እንዲጠቀም እንጂ በጭፍን እንዲታዘዝ አትፈልጉም። (ሮም 12:1, 2) ይህን እንዲያደርግ ልትረዱት የምትችሉት እንዴት ነው?

አንደኛው መንገድ የውስጡን አውጥቶ እንዲናገር ዕድል መስጠት ነው። መናገር ሲጀምር አታቋርጡት፤ እንዲሁም መስማት የማትፈልጉትን ነገር ቢናገር እንኳ ስሜታችሁን ለመቆጣጠር ሞክሩ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት” ይላል። (ያዕቆብ 1:19፤ ምሳሌ 18:13) ከዚህም በላይ ኢየሱስ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” ብሏል። (ማቴዎስ 12:34) በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘውን ልጃችሁን ትኩረት ሰጥታችሁ የምታዳምጡት ከሆነ የሚያሳስቡትን ነገሮች ማወቅ ትችላላችሁ።

የተሰማችሁን ሁሉ በቀጥታ ከመናገር ይልቅ በጥያቄዎች ለመጠቀም ሞክሩ። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን ብቻ ሳይሆን ግትር የነበሩትን ሰዎች እንኳ “እስቲ ምን ትላላችሁ?” ብሎ በመጠየቅ አመለካከታቸውን ለማወቅ የሞከረባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ማቴዎስ 21:23, 28) ልጃችሁ ከእናንተ የተለየ አመለካከት እንዳለው በሚገልጽበት ጊዜ እናንተም እንደ ኢየሱስ ማድረግ ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል፦

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያለው ልጃችሁ “አምላክ መኖሩን ማመን ይከብደኛል” ቢላችሁ

ማለት የሌለባችሁ ነገር፦ “እንዲህ ነው እንዴ ያስተማርንህ? አምላክ መኖሩንማ ማመን አለብህ!”

ልትሰጡት የምትችሉት መልስ፦ “እንዲህ እንድትል ያደረገህ ምንድን ነው?”

ልጃችሁ ሐሳቡን ይበልጥ እንዲገልጽ ማድረግ የሚኖርባችሁ ለምንድን ነው? ልጃችሁ የተናገረውን የሰማችሁት ቢሆንም ይህን ያለው ምን አስቦ እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋችኋል። (ምሳሌ 20:5) መቀበል የከበደው የአምላክን መኖር ሳይሆን እሱ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ የአምላክን የሥነ ምግባር ሕግጋት እንዲጥስ ተጽዕኖ የሚደረግበት ወጣት በአምላክ መኖር እንደማያምን በማሰብ ሕግጋቱን መጣሱ ችግር እንደሌለው ራሱን ለማሳመን ይጥር ይሆናል። (መዝሙር 14:1) ይህ ወጣት ‘አምላክ ከሌለ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቼ መኖር አያስፈልገኝም’ ብሎ ሊያስብ ይችላል።

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያለው ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለው ‘የአምላክ መሥፈርቶች እንደሚጠቅሙኝ ከልቤ አምናለሁ?’ የሚለውን ጥያቄ ሊያስብበት ይገባል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) የአምላክ መሥፈርቶች እንደሚጠቅሙት የሚያምን ከሆነ ለሚጠቅመው ነገር አቋም መውሰድ እንደሚገባው እንዲገነዘብ እርዱት።​—ገላትያ 5:1

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያለው ልጃችሁ “እኔ የእናንተን ሃይማኖት የመከተል ግዴታ የለብኝም” ቢላችሁ

ማለት የሌለባችሁ ነገር፦ “ይህ የሁላችንም ሃይማኖት ነው፤ አንተ ደግሞ ልጃችን ስለሆንክ እኛ የምንከተለውን ሃይማኖት ትከተላለህ።”

ልትሰጡት የምትችሉት መልስ፦ “ይህ ከባድ አነጋገር ነው። የእኛን እምነት የማትጋራ ከሆነ ሌላ የምታምንበት ነገር አለህ ማለት ነው። ታዲያ አንተ የምታምንባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? በአንተ አመለካከት በሕይወታችን ውስጥ መመሪያ ሊሆነን የሚችለው ትክክለኛው የሥነ ምግባር መሥፈርት የትኛው ነው?

ልጃችሁ ሐሳቡን ይበልጥ እንዲገልጽ ማድረግ የሚኖርባችሁ ለምንድን ነው? በዚህ መንገድ አሳማኝ የሆኑ ነጥቦችን እያነሳችሁ መወያየታችሁ አመለካከቱን እንዲገመግም ሊረዳው ይችላል። እንዲህ ማድረጋችሁ እሱ የሚያምንባቸው ነገሮች እናንተ ከምታምኑባቸው ጋር ተመሳሳይ እንደሆኑና ከላይ ያለውን ዓይነት ጥያቄ እንዲያነሳ ያደረገው ምክንያት ሌላ እንደሆነ እንዲገነዘብ ሊያደርገው ይችላል።

ለምሳሌ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያለው ልጃችሁ እምነቱን ለሌሎች ማስረዳት ያቅተው ይሆናል። (ቆላስይስ 4:6፤ 1 ጴጥሮስ 3:15) ወይም ደግሞ እምነቱን የማትጋራው ወጣት አፍቅሮ ይሆናል። የችግሩን መንስኤ ለማወቅና ለልጃችሁም ይህን ለማስገንዘብ ጥረት አድርጉ። ልጃችሁ በማስተዋል ችሎታው አዘውትሮ መጠቀሙ ሙሉ ሰው ሆኖ ለሚመራው ሕይወት ያዘጋጀዋል።

2 አዋቂዎች የሚሰጡት እርዳታ

አንዳንድ የሥነ ልቦና ሊቃውንት ከጉርምስና ዕድሜ ጋር ተያይዞ መምጣቱ የማይቀር እንደሆነ የሚገልጹት ‘የስሜት ነውጥና ውጥረት’ በአሁኑ ጊዜ በተወሰኑ ማኅበረሰቦች ውስጥ እምብዛም ወይም ጨርሶ አይታይም ማለት ይቻላል። በእነዚህ ማኅበረሰቦች ውስጥ ወጣቶች ወደ አዋቂነት ሕይወት የሚሸጋገሩት በልጅነታቸው እንደሆነ በመስኩ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ከትላልቅ ሰዎች ጋር ይሠራሉ፣ ውሏቸው ከአዋቂዎች ጋር ነው እንዲሁም የትልቅ ሰው ኃላፊነቶች ይሰጧቸዋል። በእነዚህ ማኅበረሰቦች ውስጥ “የወጣቶች ባሕል” እና “ወጣት ጥፋተኞች” የሚሉት አገላለጾች ሌላው ቀርቶ “ጉርምስና” የሚለው ቃል እንኳ የለም።

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ በርካታ ተማሪዎች አንድ ላይ ታጭቀው በሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚኖረውን ሁኔታ እንመልከት፤ ይህ ሁኔታ በብዙ አገሮች ውስጥ የሚታይ ሲሆን ተማሪዎቹ ተቀራርበው ሊጨዋወቱ የሚችሉት ከእኩዮቻቸው ጋር ብቻ ነው። ወደ ቤት ሲሄዱ ወላጆቻቸው ሥራ ስለሚሆኑ ባዶ ቤት ይጠብቃቸዋል። ዘመዶቻቸውም ቢሆኑ የሚኖሩት ርቀው ነው። በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከእኩዮቻቸው ጋር ነው። * እነዚህ ልጆች ምን ዓይነት አደጋ እንደሚያጋጥማቸው መገመት ትችላላችሁ? ከመጥፎ ልጆች ጋር ሊገጥሙ የሚችሉ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሌላም አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል። አርዓያ የሚሆኑ ወጣቶች እንኳ ትልልቅ ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ የማያሳድሩባቸው ከሆነ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት የመፈጸም አዝማሚያ እንደሚታይባቸው ጥናቶች ያሳያሉ።

የጥንቱ የእስራኤል ማኅበረሰብ ወጣቶችና አዋቂዎች እንዲቀራረቡ ያደርግ ነበር። * ለምሳሌ ያህል፣ ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ የይሁዳ ንጉሥ ስለሆነው ስለ ዖዝያን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ዖዝያን ይህን ከባድ ኃላፊነት እንዲወጣ የረዳው ምን ነበር? ከረዱት ነገሮች አንዱ ዘካርያስ የተባለ አዋቂ ሰው ያሳደረበት በጎ ተጽዕኖ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ዘካርያስ ለዖዝያን “እግዚአብሔርን መፍራት” እንዳስተማረው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።​—2 ዜና መዋዕል 26:5

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ እናንተ የምትመሩባቸውን መሥፈርቶች የሚከተሉ አዋቂ የሆኑ ወዳጆች አሉት? ልጃችሁ እንዲህ ካሉት በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ሰዎች ጋር በመወዳጀቱ አትቅኑ። እነዚህ ሰዎች ልጃችሁ ትክክለኛውን ጎዳና እንዲከተል ሊረዱት ይችላሉ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል” ይላል።​—ምሳሌ 13:20

3 የኃላፊነት ስሜት

በአንዳንድ አገሮች ታዳጊ ወጣቶች በሳምንት ከተወሰነ ሰዓት በላይ ተቀጥረው እንዳይሠሩ ወይም በአንዳንድ ሥራዎች እንዳይካፈሉ የሚከለክሉ ሕጎች አሉ። እንደ እነዚህ ያሉ ሕጎች የወጡት በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመን የተካሄደው የኢንዱስትሪ አብዮት ካስከተላቸው አደገኛ የሆኑ የሥራ ሁኔታዎች ልጆችን ለመጠበቅ ነው።

በልጆች ላይ የሚፈጸመውን የጉልበት ብዝበዛ ለመከላከል የወጡት ሕጎች ልጆች ለአደጋ እንዳይጋለጡና ግፍ እንዳይፈጸምባቸው ከለላ ያደረጉላቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዳይሆኑ እንዳደረጓቸው የሚናገሩ ባለሙያዎች አሉ። በዚህም ምክንያት፣ ማብቂያ ከሌለው የጉርምስና ዕድሜ ማምለጥ (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙ ወጣቶች “ማንኛውንም ነገር ማግኘት መብታቸው እንደሆነና ምንም ጥረት ሳያደርጉ ነገሮችን ሊያገኙ እንደሚገባ ይሰማቸዋል።” የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊዎች እንደገለጹት እነዚህ ወጣቶች እንዲህ ያለ ዝንባሌ ያዳበሩት “የሚኖሩበት ዓለም ከእነሱ ምንም ነገር ሳይጠብቅ ሊያስደስታቸው ብቻ ታጥቆ የተነሳ” በመሆኑ ነው።

ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ ገና በልጅነታቸው ከባድ ኃላፊነት ስለተሸከሙ ወጣቶች ይናገራል። ጢሞቴዎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ጢሞቴዎስ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደረበት ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር የተገናኘው ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ በነበረበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ በአንድ ወቅት ጢሞቴዎስን “የተቀበልከውን የአምላክ ስጦታ እንደ እሳት እንድታቀጣጥል አሳስብሃለሁ” ብሎት ነበር፤ ይህን ያለው ጢሞቴዎስ የተሰጠውን ሥራ በሙሉ ልቡና ኃይሉ እንዲያከናውን ለማበረታታት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 1:6) ጢሞቴዎስ ምናልባትም በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ በነበረበት ጊዜ ከቤተሰቦቹ ተለይቶ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በመጓዝ ጉባኤዎችን ማቋቋምና ወንድሞችን ማበረታታት ጀመረ። ጳውሎስ አሥር ዓመት ያህል ከጢሞቴዎስ ጋር ከሠራ በኋላ በፊልጵስዩስ ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች “ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ የሚጨነቅ እንደ እሱ ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝም” በማለት ጽፏል።​—ፊልጵስዩስ 2:20

አብዛኛውን ጊዜ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ኃላፊነት ለመቀበል ይጓጓሉ፤ በተለይ ደግሞ ኃላፊነቱ ሌሎችን ሊጠቅም የሚችል ትርጉም ያለው ሥራ ለማከናወን እንደሚያስችላቸው ሲያውቁ ይህን ለማድረግ ይነሳሳሉ። ይህም ወደፊት ኃላፊነት የሚሰማቸው አዋቂዎች እንዲሆኑ የሚያሠለጥናቸው ከመሆኑም ሌላ አሁንም ቢሆን ያሏቸው መልካም ባሕርያት ጎልተው እንዲታዩ ያደርጋል።

ከአዲስ “የአየር ጠባይ” ጋር መላመድ

በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ካላችሁ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበራችሁበት “የአየር ጠባይ” በተለየ ሁኔታ ውስጥ እንዳላችሁ ሳይሰማችሁ አይቀርም። ያም ቢሆን ልጃችሁ ካለፈባቸው ሌሎች የእድገት ደረጃዎች ጋር እንደተላመዳችሁ ሁሉ ከዚህኛውም የእድገት ደረጃ ጋር መላመዳችሁ እንደማይቀር እርግጠኞች ሁኑ።

ልጃችሁ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚሆንበትን ወቅት (1) የማስተዋል ችሎታውን እንዲያዳብር ለመርዳት፣ (2) የአዋቂዎችን እርዳታ እንዲያገኝ ለማድረግ እንዲሁም (3) ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እንዲሆን ለመርዳት እንደሚያስችላችሁ አጋጣሚ አድርጋችሁ ተመልከቱት። እንዲህ ካደረጋችሁ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘውን ልጃችሁን ሙሉ ሰው ለሚሆንበት ጊዜ እያዘጋጃችሁት ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.17 አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ የጉርምስና ወቅትን “ረጅም የስንብት ጊዜ” በማለት በትክክል ገልጾታል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የግንቦት 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 10-12 ተመልከት።

^ አን.38 በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆችን ትኩረት አድርገው የሚዘጋጁ መዝናኛዎች፣ ልጆቹ ከእኩዮቻቸው ጋር ለመሆን ያላቸውን ተፈጥሯዊ ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ናቸው። እነዚህ መዝናኛዎች ወጣቶች፣ አዋቂዎች ሊገባቸው የማይችል የራሳቸው የሆነ ባሕል አላቸው የሚለውን አስተሳሰብ ያስፋፋሉ።

^ አን.39 “የጉርምስና ዕድሜ” እና “የአሥራዎቹ ዕድሜ” የሚሉት አገላለጾች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኙም። በቅድመ ክርስትናም ሆነ በክርስትና ዘመን በአምላክ ሕዝቦች መካከል ይኖሩ የነበሩ ወጣቶች ወደ አዋቂነት የሚሸጋገሩት ዛሬ በብዙዎቹ ማኅበረሰቦች ውስጥ ከተለመደው የዕድሜ ክልል ቀደም ብለው ነበር።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“ወላጆቼን በማንም አልለውጣቸውም”

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወላጆች በንግግራቸውም ሆነ ምሳሌ በመሆን ልጆቻቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ያስተምሯቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) ይሁን እንጂ ይህን እንዲያደርጉ አያስገድዷቸውም። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወላጆች እያንዳንዱ ልጅ ለአካለ መጠን ሲደርስ በየትኞቹ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መመራት እንደሚፈልግ ራሱ መወሰን እንደሚኖርበት ይገነዘባሉ።

የ18 ዓመቷ አሽሊን ወላጆቿ ያስተማሯትን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ታምንባቸዋለች። እንዲህ ብላለች፦ “በሳምንት አንድ ቀን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በማከናወን ብቻ ከመወሰን ይልቅ ለሃይማኖቴ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ እሰጠዋለሁ። ከዚህም በተጨማሪ የጓደኛ ምርጫዬን፣ የምማረውን ትምህርትና የማነባቸውን መጻሕፍት ጨምሮ በማደርጋቸው ነገሮችና ውሳኔዎች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል።”

አሽሊን፣ ክርስቲያን ወላጆቿ እሷን ያሳደጉበትን መንገድ በጣም ታደንቃለች። “ወላጆቼን በማንም አልለውጣቸውም” በማለት ተናግራለች። አክላም “የይሖዋ ምሥክር የመሆን እንዲሁም ምንጊዜም የይሖዋ አገልጋይ ሆኜ የመኖር ፍላጎት እንዲያድርብኝ ስለረዱኝ በጣም ዕድለኛ ነኝ። በሕይወት እስካለሁ ደረስ ወላጆቼ ያስተማሩኝን መመሪያዎች መከተሌን አላቆምም” ብላለች።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻችሁ ስሜታቸውን እንዲገልጹ አጋጣሚ ስጧቸው

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዋቂዎች በልጃችሁ ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ልጆች ትርጉም ያለው ሥራ ማከናወናቸው ኃላፊነት የሚሰማቸው አዋቂዎች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል