በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወላጆች ግብ ምንድን ነው?

የወላጆች ግብ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የወላጆች ግብ ምንድን ነው?

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ምን ዓይነት ሰው እንዲሆን ትፈልጋላችሁ?

ሀ. የእናንተ ግልባጭ

ለ. ምንጊዜም እናንተን የሚቃረን ዓመፀኛ

ሐ.ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎችን የሚያደርግና ኃላፊነት የሚሰማው አዋቂ

ሐ ላይ የተገለጸውን የሚመርጡ አንዳንድ ወላጆች ተግባራቸው ሀ ላይ ያለውን ውጤት ለማግኘት የሚፈልጉ ይመስላል። ለአብነት ያህል፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃቸው እነሱ ትልቅ ግምት የሚሰጡትን ሙያ እንዲመርጥ በመንገር በእሱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ይሞክራሉ። ይህ ምን ያስከትላል? ልጁ ትንሽ መፈናፈኛ ሲያገኝ ወዲያውኑ በተቃራኒው አቅጣጫ መሄድ ይጀምራል። የሚገርመው ነገር፣ ሀ ላይ የተገለጸውን የሚዘሩ ብዙ ወላጆች ለ ላይ የተገለጸውን ያጭዳሉ።

መፈናፈኛ ማሳጣት ጥሩ ውጤት የማያስገኘው ለምንድን ነው?

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎችን የሚያደርግና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እንዲሆን ለመርዳት እንደምትፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ እዚህ ግብ ላይ መድረስ የምትችሉት እንዴት ነው? በእርግጠኝነት የሚታወቅ አንድ ነገር አለ፦ ልጆችን መፈናፈኛ ማሳጣት ግባችሁ ላይ ለመድረስ አያስችላችሁም። ይህን የምንልባቸውን ሁለት ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።

1. ልጆችን መፈናፈኛ ማሳጣት ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም። ይሖዋ አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም ጥሩም ሆነ መጥፎ፣ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ የመረጡትን ጎዳና እንዲከተሉ ይፈቅድላቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ቃየን ወንድሙን አቤልን ለመግደል የሚያነሳሳ የቁጣ ስሜት ባደረበት ጊዜ ይሖዋ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “መልካም ብታደርግ ተቀባይነትን አታገኝምን? መልካም ባታደርግ ግን፣ ኀጢአት በደጅህ እያደባች ናት፤ ልታሸንፍህ ትፈልጋለች፤ አንተ ግን ተቈጣጠራት።”​—ዘፍጥረት 4:7

ይሖዋ ለቃየን ግልጽ የሆነ ምክር ቢሰጠውም ምክሩን እንዲቀበል እንዳላስገደደው ልብ በሉ። ቃየን ቁጣውን ከመቆጣጠር ወይም ቁጣው እንዲቆጣጠረው ከመፍቀድ አንዱን መምረጥ ነበረበት። ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ይሖዋ ፍጡራኑ እንዲታዘዙት ሲል መፈናፈኛ ለማሳጣት የማይሞክር ከሆነ እናንተም በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁን መፈናፈኛ ማሳጣት የለባችሁም። *

2. ልጆችን መፈናፈኛ ማሳጣት ብዙውን ጊዜ መጥፎ ውጤት አለው። አንድ ነጋዴ፣ የሆነ ዕቃ እንድትገዙት ሊያሳምናችሁ እየሞከረ ነው እንበል። ዕቃውን እንድትገዙት በገፋፋችሁ መጠን ጭራሹኑ ላለመግዛት ትወስናላችሁ። ዕቃው የሚያስፈልጋችሁ ቢሆንም እንኳ እንዳትገዙት ያደረጋችሁ የእሱ ሁኔታ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም ከእሱ መገላገል ትፈልጋላችሁ።

እናንተም የምትመሩባቸውን እሴቶች፣ የምታምኑባቸውን ነገሮችና ግቦቻችሁን በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ እንዲቀበል የምታስገድዱት ከሆነ ተመሳሳይ ነገር ሊያጋጥማችሁ ይችላል። ልጃችሁ እነዚህን ነገሮች የሚቀበል ይመስላችኋል? ላይቀበል ይችላል! እንዲያውም እንዲህ ማድረጋችሁ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ የእናንተን መሥፈርቶች እንዲጠላ ስለሚያደርገው ውጤቱ ከጠበቃችሁት ተቃራኒ ሊሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን መፈናፈኛ ለማሳጣት የሚያደርጉት ጥረት አይሳካም። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘውን ልጃችሁን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ከመሞከርና ሕፃን ሳለ ታደርጉት እንደነበረው የምትመሩባቸውን እሴቶች እንዲቀበል ከማስገደድ ይልቅ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ጥበብ መሆኑን እንዲያስተውል እርዱት። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያን ከሆናችሁ ልጃችሁ የአምላክን መመሪያዎች መታዘዙ የኋላ ኋላ ትልቅ እርካታ የሚያስገኝለት እንዴት እንደሆነ አስረዱት።​—ኢሳይያስ 48:17, 18

ይህን ስታደርጉ ጥሩ ምሳሌ መሆን እንዳለባችሁ አትዘንጉ። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ እንዲሆን የምትፈልጉትን ዓይነት ሰው ሁኑ። (1 ቆሮንቶስ 11:1) የምትመሩባቸው እሴቶች በሕይወታችሁ በግልጽ እንዲታዩ አድርጉ። (ምሳሌ 4:11) ልጃችሁ ለአምላክና እሱ ላወጣቸው መሥፈርቶች ፍቅር ካዳበረ እናንተ በሌላችሁበትም እንኳ የሚያደርጋቸው ምርጫዎች ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ይሆናሉ።​—መዝሙር 119:97፤ ፊልጵስዩስ 2:12

ለልጃችሁ ጠቃሚ ክህሎቶችን አስተምሩት

በዚህ መጽሔት በገጽ 2 ላይ እንደተገለጸው ልጃችሁ አድጎ “ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ” የሚሄድበት ቀን ምናልባትም ካሰባችሁት በላይ በጣም ፈጥኖ ይደርሳል። (ዘፍጥረት 2:24) ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ልጃችሁ፣ ትልቅ ሰው ሆኖ ራሱን ችሎ በሚኖርበት ጊዜ ሊጠቅሙት የሚችሉ ክህሎቶች እንዲኖሩት ትፈልጋላችሁ። ገና ከቤት ሳይወጣ ልታስተምሩት የምትችሏቸውን አንዳንድ ክህሎቶች እንመልከት።

የቤት ውስጥ ሥራዎች፦ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ምግብ ማዘጋጀት፣ ልብሱን አጥቦ መተኮስ፣ ክፍሉን በንጽሕናና በሥርዓት መያዝ እንዲሁም የመኪናውን ደኅንነት መከታተል ብሎም ቀላል ጥገና ማድረግ ይችላል? ወንድ ወይም ሴት ልጃችሁ እንዲህ የመሰሉትን ክህሎቶች ማዳበራቸው አንድ ቀን የራሳቸውን ቤት እንዲያስተዳድሩ ያስችላቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በገዛ እጆቼ እየሠራሁ ራሴንም ሆነ ጓደኞቼን እረዳ እንደነበር እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ” ብሏል።​—የሐዋርያት ሥራ 20:34 የ1980 ትርጉም

ከሰው ጋር ተግባብቶ መኖር፦ (ያዕቆብ 3:17) በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖር ይችላል? አለመግባባቶችን ወዳጃዊ በሆነ መንገድ መፍታት ይችላል? ሰዎችን በአክብሮት እንዲይዝና ቅራኔዎችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት እንዲችል አሠልጥናችሁታል? (ኤፌሶን 4:29, 31, 32) መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ” ይላል።​—1 ጴጥሮስ 2:17

ገንዘብ አያያዝ፦ (ሉቃስ 14:28) በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ የገቢ ምንጭ የሚያገኝበት አንድ ዓይነት ሙያ እንዲማር፣ ገንዘቡን አብቃቅቶ መኖር እንዲችልና ዕዳ ውስጥ ከመግባት እንዲቆጠብ ልትረዱት ትችላላችሁ? ደግሞም የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለመግዛት ገንዘብ እንዲያጠራቅም፣ ያየውን ሁሉ ከመግዛት እንዲቆጠብና መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች ረክቶ እንዲኖር አሠልጥናችሁታል? (ምሳሌ 22:7) ጳውሎስ “ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል” በማለት ጽፏል።​—1 ጢሞቴዎስ 6:8

ትክክለኛ በሆኑ እሴቶች የሚመሩና ጠቃሚ የሆኑ ክህሎቶችን ያዳበሩ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ለወደፊቱ ሕይወታቸው ዝግጁ ናቸው። ወላጆቻቸውም ቢሆኑ ግባቸውን አሳክተዋል ሊባል ይችላል!​—ምሳሌ 23:24

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የየካቲት 1, 2011 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 18-19 ተመልከት።

ይህን አስተውለኸዋል?

● ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ግባችሁ ምንድን ነው?​—ዕብራውያን 5:14

● በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁ ትልቅ ሰው ሲሆን ምን ዓይነት ኃላፊነት መሸከም ይኖርበታል?​—ኢያሱ 24:15

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ምን ዓይነት ሰው እንዲሆን ትፈልጋላችሁ?

የእናንተ ግልባጭ

ዓመፀኛ

ኃላፊነት የሚሰማው አዋቂ