በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በታዝሜንያ ዱር የሚገኙ እንግዳ ፍጥረታት

በታዝሜንያ ዱር የሚገኙ እንግዳ ፍጥረታት

በታዝሜንያ ዱር የሚገኙ እንግዳ ፍጥረታት

የታዝሜንያ ዱር ቀን ላይ ኮሽታ የማይሰማበት ጸጥ ረጭ ያለ ቦታ ነው። ሌሊት ላይ ግን ብርክ የሚያስይዝ ጩኸትና አስፈሪ የሆነ ማጓራት ጫካው ውስጥ ያስተጋባል። የዚህ ሁሉ ሁካታ ምንጭ ምንድን ነው? ታዝሜንያን ዴቭል (የታዝሜንያ ዲያብሎስ) የሚል ደስ የማይል ስም የተሰጠው እንስሳ ነው፤ ሴቷ ዴቭል እንደ ካንጋሮ ልጆቿን የምትሸከምበት ኪስ አላት። የሚያሸብር ድምፅ ያላቸው እነዚህ ጠንካራ እንስሳት በተለይ ጥንብ አግኝተው በሚበሉበት ጊዜ ድምፃቸውም ሆነ መልካቸው በፍርሃት ያርዳል። ሆኖም ይህ ሁሉ እንዲያው ፉከራ ብቻ ነው።

እነዚህ እንስሳት በጫካው ውስጥ የሚገኘውን ጥንብ በሙሉ በሚያስደንቅ ፍጥነት ሙልጭ አድርገው ይበሉታል። ጠንካራ በሆነው ጥርሳቸው የማንኛውንም ጥንብ ቆዳም ሆነ አጥንት መቆረጣጠም ይችላሉ። እንዲያውም ታዝሜንያን ዴቭል በግማሽ ሰዓት ውስጥ የራሱን ክብደት 40 በመቶ የሚያህል ነገር ጥርግ አድርጎ መብላት ይችላል፤ ይህም አንድ ሰው 25 ኪሎ ግራም የሥጋ ጥብስ በአንድ ጊዜ ቢበላ እንደ ማለት ነው።

ከታዝሜንያን ዴቭል ይበልጥ ደስ የሚለው ግን ኮመን ዋምባት የተባለው ደልደል ያለ ቁመናና ለስላሳ ፀጉር ያለው እንስሳ ነው። እንስቷ ዋምባት አጥቢ ከመሆኗም ሌላ ግልገሏን የምትሸከምበት ኪስ አላት። ከሌሎቹ ባለ ኪስ እንስሳት በተለየ፣ እንስቶቹ ዋምባቶች ግልገሎቻቸውን የሚሸከሙበት ኪስ ወደኋላ የዞረ በመሆኑ ጎሬያቸውን በሚምሱበት ጊዜ አፈሩ ግልገሉ ላይ አይበተንም። በተጨማሪም ጥርሳቸው ማደጉን አያቆምም፤ ዋምባቶች መሬቱን በሚምሱበት ጊዜ የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ነገር ለመሰባበር ስለሚያስችላቸው ጥርሳቸው ሁልጊዜ የሚያድግ መሆኑ በጣም ይጠቅማቸዋል። ዋምባቶች ድቡልቡል ያሉ በመሆናቸው ቀርፋፋ ቢመስሉም በሚያስደንቅ መንገድ ተክሎችን በፊት እግራቸው እየቀጠፉ መመገብ ይችላሉ።

በታዝሜንያ ዱር የሚገኘው ሌላው እንግዳ ፍጥረት ፕላቲፐስ ይባላል። ይህ ያልተለመደ መልክ ያለው ፍጥረት እንደ ዳክዬ ዓይነት አፍና እግር፣ ቡናማ ፀጉር እንዳለው ትንሽ አቆስጣ ዓይነት ገላ እንዲሁም እንደ በግ ላት ጠፍጣፋ የሆነ ጅራት አለው። እነዚህ እንስሳት እንደ ዶሮ እንቁላል ይጥላሉ፣ እንደ ዋምባት መሬት ይቆፍራሉ እንዲሁም እንደ ድብ ግልገሎቻቸውን ያጠባሉ። ይህን ፍጡር ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው የሳይንስ ሊቅ እውነተኛ እንሰሳ እንዳልሆነ መጠርጠሩ ምንም አያስገርምም።

እንደነዚህ ያሉትን ፍጥረታት መመልከት የሚያስደስተን ለምንድን ነው? ፈጣሪያችን እንድንደሰትባቸው አድርጎ ስለፈጠራቸው ነው። ፈጣሪ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት “በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው” ብሏቸው እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:28) አምላክ የሰጠው ይህ ትእዛዝ በምድር ላይ ያሉትን እንስሳት መንከባከብን ይጨምራል። ታዲያ እንደነዚህ ያሉትን እንስሳት ስንመለከት ይህን ኃላፊነታችንን ለመወጣት አንነሳሳም?

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ግዙፎቹ ዛፎች

በግዝፈት ረገድ ከታዝሜንያ ትላልቅ ዛፎች ጋር ሊወዳደሩ የሚችሉ ሕያዋን ፍጥረታት በጣም ጥቂት ናቸው። በጣም ረጅም የሆኑት ማውንቴይን አሽ (ዩካሊፕተስ ሬግናንስ) የተባሉት ዛፎች ርዝመታቸው እስከ 75 ሜትር የሚደርስ ሲሆን አበባ ያወጣሉ። ከእነዚህ ዛፎች መካከል በጣም ረጅሙ 99.6 ሜትር ያህላል፤ ይህ ዛፍ በዓለም በርዝመቱ አንደኛ ከሆነውና በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኘው ሬድውድ የተባለ ዛፍ የሚያንሰው በ16 ሜትር ብቻ ነው።

ሁዎን ፓይን የሚባለው ሌላው የዱር ዛፍ ደግሞ ርዝመቱ መካከለኛ ከሚባለው ማውንቴይን አሽ በግማሽ የሚያንስ ቢሆንም እስከ ስድስት እጥፍ የሚበልጥ ዕድሜ ሊኖረው ይችላል። አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት ሁዎን ፓይን የተባሉት ዛፎች ከ3,000 ዓመት በላይ ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገምታሉ፤ ይህም ምድር ላይ ከሚገኙት ዛፎች በሙሉ በዕድሜያቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። “የታዝሜንያ ዛፎች መስፍን” ተብሎ የሚጠራው ይህ ዛፍ በቤት ዕቃዎችና በጀልባ ሠሪዎች ዘንድ በጣም ተወዳጅ ነው። ቢጫ ቀለም ያለው የዚህ ዛፍ እንጨት የተለያዩ ነገሮችን ለመሥራት አመቺ ሲሆን ምስጥ እንዳይበላውና እንዳይበሰብስ የሚከላከል የራሱ ዘይት አለው። አንዳንድ ግንዶች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ዱር ውስጥ ወድቀው የቆዩ ቢሆኑም እንኳ ዛሬም አገልግሎት ላይ ሊውሉ ይችላሉ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታዝሜንያን ዴቭል

[የሥዕል ምንጭ]

© J & C Sohns/age fotostock

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኮመን ዋምባት

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፕላቲፐስ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Wombat and platypus: Tourism Tasmania; giant tree: Tourism Tasmania and George Apostolidis