በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በማላዊ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ክንውን​—1,000 የመንግሥት አዳራሾች!

በማላዊ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ክንውን​—1,000 የመንግሥት አዳራሾች!

በማላዊ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ክንውን​—1,000 የመንግሥት አዳራሾች!

“በማላዊ ይህ ነገር ይከናወናል ብዬ በፍጹም አስቤ አላውቅም ነበር” በማለት ኦገስቲን በአድናቆት ተናግሯል። ኦገስቲን እየተናገረ የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ብለው ስለሚጠሯቸው የአምልኮ ቦታዎች ግንባታ ነው። በደቡብ ምሥራቅ አፍሪካ በምትገኘውና ትንሽ አገር በሆነችው በማላዊ በ1993 የነበሩት 30,000 የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በወቅቱ አምልኳቸውን ለማከናወንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚጠቀሙባቸው ተስማሚ የሆኑ ስፍራዎች አልነበሯቸውም።

አሁን ግን ይህ ሁኔታ በጣም ተለውጧል። በብላንታየር፣ ማላዊ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች መስከረም 2010 ላይ አንድ ሺህኛውን የመንግሥት አዳራሽ ሠርተው አጠናቀዋል! * ይሁንና በማላዊ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥራቸው 30,000 እስኪደርስ ድረስ የአምልኮ ስፍራዎችን መገንባት ያልጀመሩት ለምንድን ነው? የገንዘብ አቅማቸው ውስን የሆነው እነዚህ ወንድሞች ግንባታውን ከጀመሩ በኋላ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በአጭር ጊዜ ውስጥ 1,000 አዳራሾችን መገንባት የቻሉት እንዴት ነው? ይህ አስገራሚ የግንባታ ፕሮግራም በይሖዋ ምሥክሮችና በአካባቢያቸው በሚኖሩ ሰዎች ላይስ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል?

የመከራ ወቅት

በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው የሚጠሩት የይሖዋ ምሥክሮች በ1900ዎቹ መጀመሪያ ላይ በማላዊ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማስተማር ጀመሩ። በ1967 በማላዊ 17,000 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ ሕግንም ሆነ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በማክበራቸው ይታወቁ ነበር። በተጨማሪም እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች እነሱም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ፍጹም ገለልተኞች ነበሩ።​—ዮሐንስ 18:36፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29

የሚያሳዝነው ነገር፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው አቋማቸው በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ከመንግሥት ጋር አለመግባባት እንዲፈጠር አደረገ፤ በመሆኑም በ1967 እገዳ ተጣለባቸው። ወዲያውኑ ብዙዎች ያለምንም ምክንያት ከሥራቸው ተፈናቀሉ፤ እንዲሁም በሕገ ወጥ መንገድ ንብረታቸው ይወረስ ወይም ይወድም ነበር። በወቅቱ በተነሳው ከባድ ስደት እንዲሁም የዘር ማጥፋት ዘመቻ ይነሳል በሚል ፍርሃት በማላዊ የሚገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ጎረቤት አገሮች ማለትም ወደ ሞዛምቢክና ዛምቢያ ሸሽተዋል።

ውሎ አድሮ ግን በማላዊ የነበረው ሁኔታ በመሻሻሉ፣ ተሰደው ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አብዛኞቹ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመለሱ። እነዚህ ወንድሞች ለ26 ዓመታት ተጥሎባቸው የቆየው እገዳ ነሐሴ 12, 1993 በመነሳቱ በጣም ተደስተዋል! ይሁን እንጂ ሌላ ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጠማቸው። በዚህ ወቅት በ583 ጉባኤዎች የሚሰበሰቡት ከ30,000 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ለአምልኮ የሚሰበሰቡበት ተስማሚ ቦታ አልነበራቸውም! ታዲያ ምን ያደርጉ ይሆን?

ፍቅር በተግባር ሲገለጽ!

ከእገዳው በኋላ በነበሩት ስድስት ዓመታት በአካባቢው የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው የገንዘብ አቅም ውስን ቢሆንም የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባት ረገድ የሚያስመሰግን ሥራ አከናውነዋል። ይሁን እንጂ በየዓመቱ የሚጨምረው የይሖዋ ምሥክሮቹ ቁጥርና የሚገነቡት የመንግሥት አዳራሾች ብዛት ሊጣጣም አልቻለም። ታዲያ ምን መፍትሔ ይኖረው ይሆን? በ⁠2 ቆሮንቶስ 8:14 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ይህን ችግር ለመቅረፍ አስችሏል። በሌሎች አገሮች ያለው ትርፍ ገንዘብ እንደ ማላዊ ባሉ አገሮች ያለውን “ጉድለት እንዲሸፍን” ማድረግ ‘ሸክሙን እኩል ለመጋራት’ ያስችላል። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል፣ የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ አገሮች ውስጥ የአምልኮ ቦታዎችን ለመገንባት የሚረዳ አንድ ልዩ ዝግጅት በ1999 አቋቋመ። በማላዊ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም በዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት በመጠቀም የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ሥራቸውን በእጅጉ አፋጠኑት። *

ከዚያ በፊት በማላዊ የነበሩት ጉባኤዎች ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻቸውን በትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎች፣ በጊዜያዊ መጠለያዎች ሌላው ቀርቶ በዛፍ ጥላ ሥር ያካሂዱ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በ1,230 ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አምልኳቸውን ለማከናወንና መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር በሚያምሩ ሕንፃዎች ውስጥ ይሰበሰባሉ፤ እነዚህ ሕንፃዎች እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት የሚያገለግሉ ናቸው። በማላዊ የሚገኙት ከ75,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ዓለም ያሉ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ያደረጉላቸውን ድጋፍ እንደሚያደንቁ ምንም ጥርጥር የለውም።

እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ የአምልኮ ስፍራዎችን ሊገነቡ የቻሉት ቀለል ያሉና ለተፈለገው ዓላማ በቂ አገልግሎት የሚሰጡ አዳራሾችን ስለሚሠሩ ነው። የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ብለው የተራቀቀ ንድፍ ያላቸው ሕንፃዎችን ለመሥራት አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ ቀለል ያሉ፣ ለአምላክ ክብር የሚያመጡና የሚያምሩ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይትና ጥናት ለማካሄድ የሚመቹ ሕንፃዎችን መገንባት ይፈልጋሉ።

የአካባቢው ኅብረተሰብ ጥቅም አግኝቷል

ቀደም ሲል በማላዊ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ‘የአምልኮ ስፍራ የሌላቸው’ እየተባሉ ይፌዝባቸው ነበር። በዚህም የተነሳ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ወደ ስብሰባዎቻቸው ለመጋበዝ የሚሳቀቁበት ጊዜ ነበር። በመሆኑም የራሳቸው የሆነ የሚያምር የመንግሥት አዳራሽ ሲያገኙ ምን ያህል እንደሚደሰቱ መገመት ይቻላል። አሁን ጎረቤቶቻቸውንና ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻቸው የሚጋብዙት ደስ እያላቸው ነው። እንዲያውም በአንድ አካባቢ፣ አዲስ በተሠራ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በተደረገ ስብሰባ ላይ 698 ሰዎች በመገኘታቸው የጉባኤው አባላት በጣም ተደስተው ነበር!

በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችና ሌሎች ሰዎች በአካባቢያቸው እንዲህ ያለ ውብና በጥሩ ሁኔታ የተገነባ የመንግሥት አዳራሽ ይሠራል ብለው ፈጽሞ አስበው እንደማያውቁ ተናግረዋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኦገስቲን አንድ ጉባኤ በዛፎች ጥላ ሥር ስብሰባ ያደርግ እንደነበረ ያስታውሳል። “በበጋ ወቅት [በዚህ ሁኔታ] መሰብሰብ በጣም ደስ የሚል ነበር። በዝናብ ወቅት ግን አስቸጋሪ ነው!” በማለት ኦገስቲን ተናግሯል። ኃይለኛ ዶፍ ዝናብ በድንገት ወርዶብህ የሚያውቅ ከሆነ ኦገስቲን የጠቀሰው ችግር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገንዘብህ አይቀርም።

ኦገስቲን በአንድ ወቅት ቺምዋንጀ የሚባለውን ጉባኤ ሲጎበኝ ያጋጠመውን ነገር ያስታውሳል። እንዲህ ብሏል፦ “የእንጨት ምሰሶዎች ባሉት በሣር በተከደነ አንድ አነስተኛ መጠለያ ውስጥ ስብሰባ እያደረግን ነበር። ይሁንና ይህ በሣር የተሸፈነው የቤቱ ጣሪያ የትልልቅ መርዛማ ሸረሪቶች መኖሪያ እንደሆነ አላወቅንም ነበር። ንግግር እየሰጠሁ ሳለ በድንገት አንድ ሸረሪት ከጣራው ላይ ወርዶ እግሬ አጠገብ አረፈ! በዚህ ወቅት ከተሰብሳቢዎቹ መካከል አንዱ በድንጋጤ ‘ኦገስቲን፣ ጨፍልቀው! ጨፍልቀው!’ ብሎ ጮኸ። እኔም ወዲያውኑ ጨፈለቅኩት። በመሆኑም በሕይወት ልተርፍ ችያለሁ።” አሁን የቺምዋንጀ ጉባኤ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ያለው ሲሆን ወንድሞችና እህቶች እንዲህ ያሉ ትኩረት የሚሰርቁ ነገሮች አያጋጥሟቸውም።

‘በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለ ዕንቁ’

አስደሳች የሆነው የመንግሥት አዳራሾችን የመገንባት ፕሮግራም የይሖዋ ምሥክሮች የማኅበረሰቡን ብሎም የአካባቢውን ሹማምንት አድናቆትና አክብሮት እንዲያተርፉ እንዳደረጋቸው የሚከተሉት አስተያየቶች ይጠቁማሉ፦

✔ “የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው ፍቅርና አንድነት እንዲሁም አዲስ የአምልኮ ስፍራ መገንባቱ በማኅበረሰቡ ውስጥ እንደ ዕንቁ እንዲታዩ ያደርጋቸዋል፤ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትም የእነሱን ምሳሌ ሊከተሉ ይገባል።”​—የቻብዋንዚ አካባቢ ሹም

✔ “ከይሖዋ ምሥክሮች በጣም የማደንቀው አንድነታቸውን ነው። የእኛ ቤተ ክርስቲያን መገንባት ከተጀመረ አሥር ዓመታት ቢሆነውም እስካሁን ድረስ አልተጠናቀቀም፤ መቼ እንደሚያልቅም አይታወቅም። በአካባቢያችን እንዲህ ያለ ውብ ሕንፃ በመገንባታችሁ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።”​—የቺግዌኔምቤ መንደር አለቃ

✔ “የምትሠሩበትን መንገድ ማየት በራሱ ያስደንቃል። በጣም ፈጣኖች ብትሆኑም የምትሠሩት በጥራት ነው! በመካከላችሁ ጠንካራ አንድነት እንዳለ ይታያል።”​—የቺውዚራ አካባቢ ሹም

የመንግሥት አዳራሽ ግንባታው ፕሮግራም የቺቼዋ/ቺንያንጃ​የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት አዘጋጆችን ትኩረት እንኳ መሳብ ችሏል፤ በመዝገበ ቃላቱ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮችን አስመልክቶ “የይሖዋ ምሥክሮች በርካታ [የመንግሥት አዳራሾችን] ገንብተዋል” የሚል ሐሳብ ሰፍሯል።

“ይህን የመንግሥት አዳራሽ ማግኘታችን ተአምር ነው”

ቀደም ሲል የተጠቀሰው በብላንታየር ከተማ የሚገኘው የማኒዮዌ ጉባኤ ከጥር 30, 2011 ጀምሮ አዲሱን የመንግሥት አዳራሻቸውን ለአምላክ አገልግሎት እንዲውል አደረጉ፤ ይህ በማላዊ የተሠራው አንድ ሺህኛው የመንግሥት አዳራሽ ነው። አንድ የጉባኤው አባል “ይህን የመንግሥት አዳራሽ ማግኘታችን ተአምር ነበር። ሕልማችን እውን ሲሆን የማየት ያህል ነው” በማለት ተናግሯል።

የማኒዮዌ ጉባኤ አባል የሆነች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የግንባታ ሥራው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ አንድም ቀን ቀርቼ አላውቅም። በአካባቢያችን ተስማሚ የአምልኮ ስፍራ ሲገነባ ተሳትፎ የማድረግ መብት በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።”

ከጉባኤው ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “የመንግሥት አዳራሻችንን ለመሥራት ከአካባቢው ባለሥልጣናት ፈቃድ ለማግኘት ተቸግረን ነበር። የከተማው ባለሥልጣናት የፈቃድ ወረቀቱ ላይ ለመፈረም ብዙ ጊዜ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። ይሁን እንጂ የመንደሩ አለቃ የሆነችው ወይዘሮ ሊኔስ ቺካኦኔካ ባለሥልጣናቱ በፈቃድ ወረቀቱ ላይ እንዲፈርሙ ለማሳመን ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች።”

አንድ ቀን፣ የጉባኤው ሽማግሌ የፈቃድ ወረቀቱን ለማስፈረም ሲሄድ ወይዘሮ ቺካኦኔካም አብራው ሄደች። ከዚያም ለባለሥልጣኑ እንዲህ አለችው፦ “የይሖዋ ምሥክሮች በመንደሬ ውስጥ የመንግሥት አዳራሻቸውን እንዲሠሩ እፈልጋለሁ። እነሱ ጥሩ ሰዎች ናቸው። በመንደራችን ፍርድ ቤት ውስጥ ከእነሱ ጋር በተያያዘ ለፍርድ የቀረበ አንድም ጉዳይ አጋጥሞኝ አያውቅም።” በዚህ ወቅት ባለሥልጣኑ በወረቀቱ ላይ ፈረመ።

ወይዘሮ ቺካኦኔካ የመንግሥት አዳራሹ ለአምላክ አገልግሎት ሲወሰን በጣም ተደስታ ነበር። “በመንደሬ ውስጥ ይህ ውብ ሕንፃ በመሠራቱ ከፍተኛ ደስታና ኩራት ይሰማኛል!” ብላለች።

በመላው ማላዊ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችና በአካባቢያቸው የሚኖሩ ሰዎች ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታው ፕሮግራም ያላቸውን አድናቆት እየገለጹ ነው። በማላዊ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የራስን ጥቅም በመሠዋትና ጠንክሮ በመሥራት ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው፤ በመሆኑም በ1993 የነበረውን ያህል አሁን ከፍተኛ የመንግሥት አዳራሽ እጥረት የለባቸውም። እውነት ነው፣ ሰዎች ለአምላክ ‘መንግሥት ምሥራች’ ጥሩ ምላሽ ሲሰጡና አዳዲስ ጉባኤዎች ሲቋቋሙ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾችን መሥራት እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 24:14) በመሆኑም በማላዊ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የእምነት አጋሮቻቸው በደግነት ተነሳስተው የሚያደርጉትን ድጋፍና የልግስና መዋጮ ያደንቃሉ። *

ይሁን እንጂ በማላዊ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከሁሉም በላይ የሚያመሰግኑት አምላካቸውን ይሖዋን ነው። መዝሙራዊ እንደሚከተለው በማለት የተናገረው ሐሳብ የእነሱንም ስሜት ይገልጻል፦ “ጌታ ሆይ፤ አንተ የሠራሃቸው ሕዝቦች ሁሉ፣ መጥተው በፊትህ ይሰግዳሉ፤ ለስምህም ክብር ይሰጣሉ፤ አንተ ታላቅ ነህና፤ ታምራትም ትሠራለህ።”​—መዝሙር 86:9, 10

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት አዳራሾቹ ቁጥር ከ1,030 በላይ ሆኗል።

^ አን.9 የይሖዋ ምሥክሮች፣ በዓለም ዙሪያ የገንዘብ አቅማቸው ውስን በሆኑ 151 አገሮች ውስጥ ከ1999 አንስቶ 23,786 የመንግሥት አዳራሾችን ገንብተዋል።

^ አን.28 በመላው ዓለም የሚካሄደው የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ሙሉ በሙሉ የሚደገፈው በፈቃደኝነት በሚደረግ የገንዘብ መዋጮ ነው።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት የነበሩት የመሰብሰቢያ ስፍራዎች በአብዛኛው የሣር ክዳን ያላቸው መጠለያዎች ነበሩ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ጉባኤዎች እንዲህ ባሉ የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ይሰበሰባሉ