በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አመሰግናለሁ! ማለትን አትርሳ

አመሰግናለሁ! ማለትን አትርሳ

አመሰግናለሁ! ማለትን አትርሳ

አመሰግናለሁ የሚል የጽሑፍ መልእክት ለመጨረሻ ጊዜ የደረሰህ መቼ ነው? አንተስ እንዲህ ዓይነት መልእክት ለመጨረሻ ጊዜ የላከው መቼ ነው?

በኢንተርኔት መልእክት መለዋወጥ የሚቻልባቸው በርካታ መንገዶች ባሉበት በዚህ ዘመን በእጅ የተጻፉ የምስጋና መልእክቶችን መላክ እየቀረ መጥቷል። ሆኖም “አመሰግናለሁ” የሚል በእጅ የተጻፈ መልእክት መላክ ሰዎች ላደረጉልህ ደግነት ያለህን አድናቆት የምታሳይበት ልዩ መንገድ ነው። ምስጋናህን በዚህ መንገድ እንዴት መግለጽ እንደምትችል የሚጠቁሙ አንዳንድ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

1. ሐሳብህን በእጅህ ብትጽፍ ይበልጥ ጥሩ ነው።

2. የግለሰቡን ስም ጻፍ።

3. ስጦታ ተልኮልህ ከሆነ ስጦታው እንደደረሰህና ለምን ዓላማ ልትጠቀምበት እንዳሰብክ ጻፍ።

4. መልእክትህን ጽፈህ ስትጨርስ ምስጋናህን በድጋሚ ግለጽ።

የምስጋና መልእክት መላክህ ግለሰቡ ጥሩ ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል።

እንግዲያው በሚቀጥለው ጊዜ አንድ ሰው በእንግድነት ሲቀበልህ፣ በደግነት ተነሳስቶ አንድ ነገር ሲያደርግልህ ወይም ስጦታ ሲሰጥህ ያደረገውን ነገር ከፍ አድርገህ እንደምትመለከት ግለጽለት። አመሰግናለሁ! ማለትን አትርሳ።

[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ለውድ አክስቴ ሜሪ (2)

ስለሰጠሽኝ ሰዓት በጣም አመሰግናለሁ! (3) ብዙውን ጊዜ ተኝቼ የማርፈድ ችግር ስላለብኝ ይህ ማንቂያ ደወል ያለው ሰዓት በጣም ጠቅሞኛል። ባለፈው ሳምንት ስለተገናኘን እጅግ ደስ ብሎኛል፤ በሰላም ቤትሽ እንደገባሽ ተስፋ አደርጋለሁ። ዳግመኛ የምንገናኝበትን ጊዜ በናፍቆት እጠባበቃለሁ።

ስለ አሳቢነትሽ በድጋሚ አመሰግናለሁ! (4)

ያንቺው፣

ጆን

[ሥዕል]

(1)

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጠቃሚ ምክሮች

● የገንዘብ ስጦታዎችን ስትጠቅስ በተዘዋዋሪ ይሁን። ለምሳሌ ያህል፣ የተላከልህን የገንዘብ መጠን በቀጥታ ከመጥቀስ ይልቅ “ለላክልኝ ስጦታ አመሰግናለሁ። ገንዘቡን . . . ላደርግበት አስቤያለሁ” ልትል ትችላለህ።

● የምስጋና መልእክት በምትጽፍበት ወቅት መግለጽ የሚኖርብህ ስለ ስጦታውና ስጦታውን በማግኘትህ ስለተሰማህ የአድናቆት ስሜት ብቻ መሆን ይኖርበታል። ለምሳሌ ስላሳለፍከው የእረፍት ጊዜ ወይም በቅርቡ ወደ ሆስፒታል ስለሄድክበት ምክንያት በዚህ የምስጋና መልእክት ላይ ማካተት አይኖርብህም።

● ከስጦታው ጋር በተያያዘ ቅር ያለህ ነገር ቢኖር በፍጹም መጥቀስ አይኖርብህም። ለምሳሌ ያህል፣ “ስለ ሰጠሽኝ ሸሚዝ አመሰግናለሁ፤ ሆኖም ሸሚዙ በጣም ሰፍቶኛል!” ብሎ መጻፍ ደግነት የጎደለው ነገር ነው።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መጽሐፍ ቅዱስ አመስጋኝ እንድንሆን ያበረታታል። (ሉቃስ 17:11-19) እንዲሁም “ያለማቋረጥ ጸልዩ” የሚል ምክር ከሰጠን በኋላ “ስለ ሁሉም ነገር አመስግኑ” በማለት ይናገራል።​—1 ተሰ. 5:17, 18