በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓመፅ የማይጎዳው ሰው የለም

ዓመፅ የማይጎዳው ሰው የለም

ዓመፅ የማይጎዳው ሰው የለም

ዓመፅ የማይነካው ሰው ማን ነው? ዘወትር በዜና ዘገባዎች ላይ ዓመፅ እናያለን። በጎዳናዎች ላይና በሥራ ቦታ ዓመፅ እንዳይፈጸምብን እንፈራለን፤ እንዲሁም ልጆች በትምህርት ቤት ውስጥ ጉልበተኞች ጥቃት ያደርሱባቸዋል። በአብዛኛው ከስጋት ነፃ የሆነ ቦታ እንደሆነ በሚታሰበው በቤት ውስጥም እንኳ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በተለይም ሴቶች የደኅንነት ስሜት አይሰማቸውም። እንዲያውም አኃዙ ከአገር ወደ አገር ይለያይ እንጂ እስከ 70 በመቶ የሚደርሱ ሴቶች በወንድ ጓደኛቸው ወይም በትዳር አጋራቸው ጥቃት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

በብዙ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች፣ ፖለቲካዊ ወይም ሕዝባዊ ዓመፅ እንዳይቀሰቀስ አልፎ ተርፎም የአሸባሪዎች ጥቃት እንዳይደርስ ይፈራሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም የአሸባሪዎች ዒላማ በሆኑ አገሮች በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አማካኝነት የሚደረገው ክትትል እየጨመረ መምጣቱ የዚህን እውነተኝነት ያረጋግጣል።

በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚው እያሽቆለቆለ ቢሆንም ለክትትል የሚረዱ የቪዲዮ መሣሪያዎች ገበያ እየደራ መምጣቱ ምንም አያስገርምም። ለዚህ ሁሉ የሚሆን ገንዘብ የሚገኘው ከየት ነው? ዞሮ ዞሮ ከእኛው ነው፤ ገንዘቡ የሚሰበሰበው በግብር መልክ አሊያም በአገልግሎት ክፍያዎች አማካኝነት ነው። ከደኅንነት ጋር የተያያዙ መሣሪያዎች በጣም እየተራቀቁ መምጣታቸው እንዲሁም ዓይነታቸውና ብዛታቸው እየጨመረ መሄዱ ብሎም ዋጋቸው እየናረ መምጣቱ ለዚህ ጉዳይ የሚወጣው ወጪ እንዲያሻቅብ አድርጎታል።

ዓመፅ የሚያስከትላቸው መጥፎ ውጤቶች እስከ ዛሬ ስንከተላቸው የነበሩትን የሥነ ምግባር ደንቦችና መመሪያዎች ቆም ብለን እንድናስብ ሊያደርጉን ይገባል። በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመለከታለን፦ መገናኛ ብዙኃን ዓመፅ እንዲስፋፋ በማድረግ ረገድ ምን አስተዋጽኦ አድርገዋል? ለዓመፅ ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው? እንዲህ ከመሰሉ ጎጂ ተጽዕኖዎች ራሳችንን መጠበቅ የምንችለውስ እንዴት ነው?