በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለዓመፅ መንስኤ የሆኑ ነገሮች

ለዓመፅ መንስኤ የሆኑ ነገሮች

ለዓመፅ መንስኤ የሆኑ ነገሮች

የዓመፅ መንስኤዎች ውስብስብ ናቸው። ምክንያቶቹ ብዙ ሊሆኑ ስለሚችሉ በአንድ ነገር ላይ ብቻ ማነጣጠር ማለትም ከመጥፎ ሰዎች ጋር መዋል ወይም መዝናኛ አሊያም የአካባቢው ማኅበረሰብ እንደሆነ ብቻ ማሰብ አይቻልም። ቀጥሎ የቀረቡትን ጨምሮ በርካታ መንስኤዎች ሊኖሩ ይችላሉ።

አጣብቂኝ ውስጥ መግባትና ተስፋ መቁረጥ፦ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ጭቆና ሲደርስባቸው፣ መድልዎ ሲፈጸምባቸው፣ ከማኅበረሰቡ ሲገለሉ ወይም ለመኖር የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች ሲያጡ አሊያም ሕይወታቸውን መምራት እንዳቃታቸው ሲሰማቸው ዓመፅን እንደ መጨረሻ አማራጭ ሊጠቀሙ ይችላሉ።

የብዙኃኑን ስሜት መከተል፦ በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ በአብዛኛው እንደሚታየው ሰዎች በቡድን ሲሆኑ ወይም ከረብሸኞች ጋር ሲቀላቀሉ መጥፎ ምግባር ለማሳየት ይበልጥ ድፍረት ያገኛሉ። ለምን? ሶሻል ሳይኮሎጂ የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚናገረው ከሆነ እነዚህ ሰዎች “የሚመሩባቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ትተው ዓመፀኝነትና ቁጣ የሚንጸባረቅበትን የብዙኃኑን አመለካከት” ወደ መከተል ያዘነብላሉ። አንድ ሌላ ምንጭ እንደገለጸው ከሆነ እንዲህ ያሉት ግለሰቦች “ምንም ዓይነት ኃላፊነት ስለማይሰማቸው” እንደ አሻንጉሊት በራሳቸው ማሰብ የማይችሉ ይሆናሉ።

ጥላቻና ቅናት፦ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን የነፍስ ግድያ የፈጸመው ቃየን የተባለው ሰው ነው። (ዘፍጥረት 4:1-8) ቃየን የቁጣ ስሜቱን እንዲቆጣጠር አምላክ ቢያስጠነቅቀውም እንዲሁም ይህን ካደረገ እንደሚባርከው ቃል ቢገባለትም ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም፤ በመሆኑም በቅናትና በጥላቻ ተነሳስቶ ወንድሙን ገደለው። “ቅናትና ምቀኝነት ባለበት ሁሉ ብጥብጥና መጥፎ ነገር ሁሉ አለ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በእርግጥም እውነት ነው!​—ያዕቆብ 3:16

አልኮልና ዕፆች፦ ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን አላግባብ መጠቀም የአካልና የአእምሮ ጤንነትን የሚያቃውስ ከመሆኑም በላይ በአንጎል ውስጥ ያሉት መቆጣጠሪያ ክፍሎች በትክክል እንዳይሠሩ ያደርጋል። ይህ ደግሞ አንድ ሰው ዓመፅ ወደ መፈጸም እንዲያዘነብልና የሚያስቆጣ ነገር ሲያጋጥመው በቀላሉ ቱግ እንዲል ያደርገዋል።

ደካማ የፍትሕ ሥርዓት፦ መክብብ 8:11 “በወንጀል ላይ ባፋጣኝ ፍርድ ካልተሰጠ፣ የሰዎች ልብ ክፉን በማድረግ ዕቅድ ይሞላል” በማለት ይናገራል። የፍትሕ ሥርዓት ደካማ፣ ብቃት የሌለው ወይም ብልሹ መሆኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዓመፅ እንዲቀሰቀስ ያደርጋል።

የሐሰት ሃይማኖት፦ የተለያየ እምነት ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጠረውን ግጭትና ሽብርተኝነትን ጨምሮ በበርካታ የዓመፅ ድርጊቶች ውስጥ የሃይማኖት እጅ አለበት። ይሁን እንጂ ተወቃሾቹ ጭፍን፣ ጽንፈኛና አክራሪ የሆኑ ሰዎች ብቻ አይደሉም። ለምሳሌ፣ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ወቅት ክርስቲያን እንደሆኑ በሚናገሩም ሆነ ከክርስትና ውጭ በሆኑት ዋና ዋና ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች እርስ በርሳቸው የተራረዱ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜም መንፈሳዊ መሪዎቻቸው ለእነዚህ ጦርነቶች ቡራኬ ሰጥተዋል። እንዲህ ዓይነቱ አድራጎት አምላክን የሚያሳዝን ነው።​—ቲቶ 1:16፤ ራእይ 17:5, 6፤ 18:24

ዓመፅን የሚደግፉ ወይም የሚያበረታቱ ብዙ ነገሮች ከመኖራቸው አንጻር በዚህ ዓለም ውስጥ ሰላማዊ ሰው መሆን ይቻላል? አዎ ይቻላል፤ ይህን ቀጥሎ እንመለከታለን።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዓመፅ የሚጀምረው ከውስጣችን ነው

ለዓመፅ መንስኤ የሚሆኑ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም እንዲህ ያለው ባሕርይ በዋነኝነት የሚመነጨው ከውስጣችን ነው። ይህ የሆነው እንዴት ነው? የሰዎችን ልብ በጥልቀት የሚያውቀው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “ከሰው ልብ ክፉ ሐሳብ ይወጣል፦ ዝሙት፣ ሌብነት፣ ግድያ፣ ምንዝር፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ማታለል፣ ብልግና፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ሞኝነት።” (ማርቆስ 7:21, 22) በተደጋጋሚ መጥፎ ነገሮችን የምንመለከት ወይም የምናዳምጥ አሊያም የምናስብ ከሆነ እንዲህ ያሉ መጥፎ ዝንባሌዎች በውስጣችን ሊያቆጠቁጡ ይችላሉ።​—ያዕቆብ 1:14, 15

በሌላ በኩል ደግሞ አእምሯችንን በገጽ 8 ላይ የተገለጹትን ዓይነት ጥሩ ነገሮች የምንመግበው ከሆነ መልካም ባሕርያትን እያዳበርን እንመጣለን፤ መጥፎ ምኞቶችን የሚያቀጣጥሉ ነገሮችን ወደ አእምሯችን ስለማናስገባ እንዲህ ያሉ ዝንባሌዎችን ‘እንገድላለን።’ (ቆላስይስ 3:5፤ ፊልጵስዩስ 4:8) እንዲህ ስናደርግ አምላክ ‘ውስጣዊው ሰውነታችንን በማጠንከር’ ይረዳናል።​—ኤፌሶን 3:16

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዓመፅ ባለሙያዎችን ግራ አጋብቷቸዋል

በአንዳንድ አገሮች የሚመዘገቡት የግድያ ወንጀሎች ብዛት ከሌሎቹ በ60 እጥፍ የሚበልጠው ለምንድን ነው? ጦርነቶችና ሌሎች የዓመፅ ድርጊቶች ከሰው ልጅ ታሪክ ተለይተው የማያውቁት ለምንድን ነው? ግራ የሚያጋቡ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፤ አጥጋቢ መልስ ማግኘት ግን አልተቻለም።

አንዳንድ ተመራማሪዎች ለዓመፅ መቀስቀስ ምክንያቱ ድህነትና የሀብት አለመመጣጠን እንደሆነ ያምናሉ። አንዳንድ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚገልጹት ከሆነ የራስን ሕይወት ማጥፋትን ጨምሮ በዓመፅ ምክንያት ከሚደርሰው ሞት ውስጥ 90 በመቶ ገደማ የሚሆነው የሚፈጸመው ሀብታም ባልሆኑ አገሮች ውስጥ ነው፤ እንዲሁም በአብዛኛው በከተሞች ውስጥ ወንጀል በብዛት የሚፈጸመው ድህነት ባጠቃቸው ሰፈሮች ነው። በእርግጥ ድሃ ሰዎች ከሌሎቹ ይበልጥ ዓመፀኞች ናቸው? ወይስ በእነዚህ አካባቢዎች ብዙ ዓመፅ የሚፈጸመው ማኅበረሰቡ ሕግ የማስከበር አቅሙ ውስን በመሆኑ ነው? በዚህ ረገድ አንድ ዓይነት ድምዳሜ ላይ እንዳንደርስ የሚያደርገን በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦች የሚኖሩባት በሕንድ ውስጥ ያለችውን ካልካታን በመሰሉ ቦታዎች ያለው ሁኔታ ነው። ካልካታ በዓለም ውስጥ ካሉ የግድያ ወንጀል ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ ከሆኑ ቦታዎች አንዷ ናት።

ሌሎች ደግሞ ‘እንደ ሽጉጥ ያሉ መሣሪያዎች እንደ ልብ መገኘታቸው በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ዓመፅ ይበልጥ እንዲስፋፋ ያደርጋሉ’ የሚል መላ ምት ያቀርባሉ። ዓመፀኛ ሰዎች መሣሪያ መታጠቃቸው ይበልጥ አደገኛ እንደሚያደርጋቸው አይካድም። ይሁን እንጂ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ውስጥ ዓመፅ የሚፈጽሙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? በዚህ ጉዳይ ላይም ቢሆን ባለሙያዎች ሊስማሙ አልቻሉም።