በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓመፅ እወድ ነበር

ዓመፅ እወድ ነበር

ዓመፅ እወድ ነበር

ሳልቫዶር ጋርዛ እንደተናገረው

በልጅነቴ ዓመፅ እወድ ስለነበር ካበሳጨኝ ሰው ጋር ሁሉ እደባደብ ነበር። በአካባቢያችን የሚኖር የቦክስ ሻምፒዮና የሆነ አንድ ሰው ይህን ስላስተዋለ የቦክስ ጨዋታ አስተማረኝ። ከጊዜ በኋላ፣ ፕሮፌሽናል ቦክሰኛ በመሆን በመላው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እየተዘዋወርኩ መጋጠም ጀመርኩ። በኋላም የወሮበሎች ቡድን አባል ለሆነ አንድ ሰው የግል ጠባቂ ሆኜ ሠርቻለሁ።

ትዳር ከመሠረትኩና ስድስት ልጆች ከወለድኩ በኋላም እንኳ ለዓመፅ የነበረኝ ፍቅር አልቀነሰም። በዚያን ጊዜ የምሽት ክበብ ቤት ነበረኝ። ብዙ ጊዜ ሰዎች ሊገድሉኝ ሞክረው የነበረ ቢሆንም እኔ ግን እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት ያስደስተኝ ነበር። በአንድ ወቅት በተነሳ ጠብ ምክንያት ሁለት ሰዎችን በጥይት መትቼ ክፉኛ አቆሰልኳቸው። እንዲያውም በሌላ ጊዜ እኔና ጓደኞቼ አንድ ታዋቂ ፖለቲከኛ አግተን ለመያዝ አቅደን ነበር። ይሁን እንጂ ፖሊሶች ሴራችንን ስለደረሱበት ተይዤ ታሰርኩ። ፖሊሶች ግብረ አበሮቼን ለመያዝ በሚጥሩበት ወቅት በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሁሉም ጓደኞቼ ተገደሉ። ስለዚህ በወቅቱ እስር ቤት መሆኔ ጥሩ ሆነልኝ!

ዓመታት ካለፉ በኋላ ከእስር ቤት ተለቀቅኩ፤ ከዚያም ሥራ ፈልጌ ተቀጠርኩ። አንድ ቀን ከሥራ ወደ ቤት ስመለስ ዝልፍልፍ የሚያደርግ ራስ ምታት በድንገት ያዘኝ። በጣም ስለተጨነቅኩ አምላክ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። በወቅቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ታጠና የነበረችው ባለቤቴ ዶሎረስ አምላክ ስም እንዳለውና ስሙም ይሖዋ እንደሆነ ነገረችኝ። (መዝሙር 83:18 NW) ስለዚህ ስሙን ጠቅሼ ወደ እሱ ጸለይኩ።

ከሕመሜ ካገገምኩ በኋላ ዶሎረስ የይሖዋ ምሥክሮች በመንግሥት አዳራሻቸው በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ እንድገኝ አበረታታችኝ። የይሖዋ ምሥክሮች ደግነትና ልባዊ አሳቢነት ሲያሳዩኝ ዓይኖቼ እንባ አቀረሩ። በዚህም የተነሳ እኔም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ፤ እንዲሁም ለሕይወት ያለኝ አመለካከት ሙሉ በሙሉ መቀየር ጀመረ። የምማረውን ነገር ወደድኩት።

ይሁን እንጂ የግልፍተኝነት ጠባዬን ለመቆጣጠር ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶብኛል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ቀን ከጓደኛዬ ከአንቶኒዮ ጋር ከቤት ወደ ቤት እየሰበክን ሳለን አንድ የሚሳደብ ሰው አጋጠመን። በጣም ስለተናደድኩ ለመደባደብ ወደ እሱ ተጠጋሁ። ደግነቱ ሌላ እርምጃ ከመውሰዴ በፊት አንቶኒዮ ያዘኝ። በኋላም አንቶኒዮ፣ ኢየሱስ ስድብና ፌዝ ሲደርስበት ችሎ እንዳለፈ አስታወሰኝ። ከኢየሱስ ጋር አብሮ ያገለገለው ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:23) እነዚህ ቃላት ልቤን ነኩት።

ባለፉት ዓመታት ያደረግኋቸውን ለውጦች መለስ ብዬ ሳስብ ይሖዋ፣ ራሳችንን እንድንገዛና ሰላማዊ ሰዎች እንድንሆን የሚረዳንን መንፈስ ቅዱስ ስለሰጠኝ ምንጊዜም አመሰግነዋለሁ። (ገላትያ 5:22, 23) ቤተሰቤ አንድነት ያለውና ደስተኛ ከመሆኑም በላይ ሰላማዊና የተረጋጋ ሕይወት ማግኘት ችለናል። በተጨማሪም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ የማገልገል መብት በማግኘቴ ሌሎች ሰዎችም የአምላክን ሰላም እንዲያገኙ እየረዳሁ ነው።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳልቫዶር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመራ ረድቶታል