በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ከዋክብት በሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ?

ከዋክብት በሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ?

ይህ ሰው ይወደኛል?

ዛሬ ብጓዝ ይሻላል?

ያንን ሥራ አገኝ እሆን?

ብዙ ሰዎች ከላይ ለቀረቡት ዓይነት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ወደ ኮከብ ቆጠራ ዘወር ይላሉ። * ይሁንና ከዋክብት በእርግጥ በሕይወትህ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ? ደግሞስ ስለ ወደፊቱ ሕይወትህ ወይም ስለ ራስህ ማንነት እንድታውቅ ሊረዱህ ይችላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

ከዋክብት በወደፊቱ ሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ?

አንዳንድ ሰዎች ከተወሰነልን ዕድል ማምለጥ እንደማንችል ያምናሉ። ሰዎች ወደፊት የሚያጋጥማቸው ነገር አስቀድሞ እንደተጻፈና ከዋክብት ደግሞ የተጻፈውን መግለጥ እንደሚችሉ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ከዚህ የተለየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ለሰዎች ምርጫ እንደሰጣቸው ይናገራል፤ በመሆኑም የሚደርስባቸውን ነገር በመቆጣጠር ረገድ የተወሰነ ድርሻ አላቸው ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ለእስራኤላውያን “ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ” በማለት ነግሯቸው ነበር።—ዘዳግም 30:19

በዚህ መንገድ ይሖዋ አምላክ ለእስራኤላውያን የወደፊት ሕይወታቸውን በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው በግልጽ ነግሯቸዋል። ትእዛዛቱን ካከበሩ ብዙ በረከቶች ያገኛሉ። ሳይታዘዙ ከቀሩ ደግሞ በራሳቸው ላይ መከራ ያመጣሉ።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የእያንዳንዱ እስራኤላዊ የወደፊት ዕጣ አስቀድሞ በከዋክብት ላይ ተጽፎ ከነበረ አምላክ ሕይወትን እንዲመርጡ ማሳሰቡ ትርጉም ይኖረዋል? ደግሞስ ምንም ሊቆጣጠሩት በማይችሉት ነገር እነሱን ተጠያቂ ማድረጉ ተገቢ ይሆናል?

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርት ግልጽ ነው፦ የምንከተለው የሕይወት ጎዳና የተመካው በከዋክብት ላይ ሳይሆን በምናደርጋቸው ምርጫዎች ላይ ነው።—ገላትያ 6:7

ከዋክብት በእኛ ማንነት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ?

አብዛኞቹ ኮከብ ቆጣሪዎች የሰው ሕይወት አስቀድሞ ተወስኗል የሚለውን አመለካከት ያጣጥላሉ። አንድ ኮከብ ቆጣሪ “ዕጣ ፈንታችንን የምንወስነው እኛው ራሳችን ነን” በማለት ተናግሯል። ሆኖም ንግግሩን ሲቀጥል “በሌላ በኩል የምንወለድበት ቀን በእኛ ማንነት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል” ብሏል። ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ እምነት አላቸው። እነዚህ ሰዎች፣ ከዋክብትና ፕላኔቶች በምድራችን ላይ ግልጽ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ከሆነ በሰዎችም ላይ ምትሃታዊ ተጽዕኖ እንዴት አይኖራቸውም? ብለው ያስባሉ። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው አካልና ስለ አጽናፈ ዓለም እያንዳንዱን ጉዳይ በዝርዝር የሚያብራራ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ አይደለም። ይሁን እንጂ ይሖዋ በሰማይ ያሉትን አካላት የፈጠረው ለምን ዓላማ እንደሆነ ይገልጻል። ዘፍጥረት 1:14, 15 እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር፣ ‘ቀኑን ከሌሊት እንዲለዩ፣ የዓመት [ወቅቶችን] . . . እንዲያመለክቱ፣ ለምድር ብርሃን የሚሰጡ ልዩ ልዩ ብርሃናት በሰማይ ይሁኑ’ አለ።”

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አምላክ ከዋክብት በእኛ ማንነት ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ አድርጎ ከፈጠራቸው ይህን አይነግረንም ነበር?

ከዚህ በመነሳት ምን ብለን መደምደም እንችላለን? ከዋክብት አምላክ ከፈጠራቸው ነገሮች መካከል የሚገኙ ቢሆኑም በእኛ ማንነት ላይ ግን ተጽዕኖ አያሳድሩም።

ከሁሉ የሚሻለው መንገድ

ስለ ወደፊቱ ሕይወታችን ወይም ስለ ራሳችን ማንነት ለማወቅ የምንፈልግ መሆኑ መልካም ነው። ይሁን እንጂ ወደ ከዋክብት ከመመልከት ይልቅ ለዚህ የሚረዳን የተሻለ ነገር አለ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ አምላክ “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው” እንደሚናገር ይገልጻል። (ኢሳይያስ 46:10) ይሖዋ ዓላማ አለው፤ ደግሞም ዓላማውን ዳር ያደርሳል። (ኢሳይያስ 55:10, 11) መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ስለ አምላክ ዓላማ ማወቅ እንችላለን። በተጨማሪም ይህ ጥንታዊ ቅዱስ መጽሐፍ ሥቃይ የሚደርስብን ለምን እንደሆነና አምላክ በሰው ዘር ላይ የሚደርሱትን ችግሮች እንዴት እንደሚያስወግድ ይገልጻል። *2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1-4

ስለ ራሳችን ለማወቅና ባሕርያችንን ለማሻሻል መመሪያ ልናገኝበት የምንችለው ከሁሉ የተሻለ የእርዳታ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን ራሳችንን በሐቀኝነት እንድንመረምር ስለሚረዳን ነው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ አምላክ “ሩኅሩኅ፣” “ለቍጣ የዘገየ” እንዲሁም “ይቅር ባይ” እንደሆነ ይናገራል። (ዘፀአት 34:6፤ መዝሙር 86:5) ታዲያ እኛ በዚህ ረገድ እንዴት ነን? መጽሐፍ ቅዱስ የተሳሳተ አስተሳሰባችንን እንድንገነዘብና ምን ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልገን እንድናስተውል ይረዳናል።

ስለዚህ ስለ ወደፊቱ ሕይወታችን ወይም ስለ ራሳችን ማንነት ለማወቅ ወደ ከዋክብት መመልከት አያስፈልገንም። ከሁሉ የተሻለ እርዳታ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ይኖርብናል፤ ይህ መጽሐፍ “በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናት” ይጠቅማል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

^ አን.6 ኮከብ ቆጠራ በፀሐይ፣ በጨረቃ፣ በፕላኔቶችና በከዋክብት ላይ የሚካሄድ ጥናት ነው፤ ደግሞም እነዚህ በሰማይ ያሉ አካላት በእኛ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩና ስለ ራሳችን ማንነት እንድናውቅ ሊረዱን እንደሚችሉ ይታመናል።

^ አን.19 ስለ አምላክ ዓላማ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3⁠ን ተመልከት።