በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትዕግሥት ማጣት ጎጂ ሊሆን ይችላል

ትዕግሥት ማጣት ጎጂ ሊሆን ይችላል

እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት፦ አንድ ሰው ሁለት መኪኖች ብቻ በሚያሳልፍ መንገድ ላይ እየነዳ ነው፤ ሌላ መኪና ደርቦ ማለፍ የማይፈቀድበት ቦታ ላይ ሲደርስ ከፊቱ ሌላ መኪና ነበረ። መኪናውን የምታሽከረክረው ሴት የምትነዳው ያን ያህል ዝግ ብላ ባይሆንም ሰውየው ትዕግሥት ስላጣ እንደ ዔሊ እየተጎተተች እንደሆነ ተሰማው። ለጥቂት ደቂቃዎች ያህል በጣም ተጠግቷት ሲነዳ ከቆየ በኋላ ትዕግሥቱ ስላለቀ በከፍተኛ ፍጥነት እየነዳ አለፋት። ይህን ሲያደርግ ሕግ የጣሰ ከመሆኑም ሌላ አደጋ ሊያስከትል ይችል ነበር።

እንደ እሷ ፈጣን ወይም ቀልጣፋ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ለመሥራት ትዕግሥት ስለሌላት ሴትስ ምን ማለት ይቻላል? አሊያም በር አንኳኩቶ እስኪከፈትለት ለመጠበቅ ትዕግሥት ስለሚያጣ ደጋግሞ የሚያንኳኳ ወይም አሳንሰሩ እስኪመጣ መጠበቅ ስለሚያቅተው የመጥሪያውን ቁልፍ ደጋግሞ የሚጫን ሰውስ? አንተስ ብዙውን ጊዜ አረጋውያን ወላጆችህን መታገሥ ይከብድሃል? ወይም ደግሞ ትናንሽ ልጆችህን በትዕግሥት መያዝ ያቅትሃል? ሌሎች የሚሠሩት ስህተት ቶሎ ያበሳጭሃል?

ሁሉም ሰው አልፎ አልፎ ትዕግሥቱ ማለቁ የማይቀር ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚፈጠረው በየቀኑ ከሆነ ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

የጤና ችግሮች፦

ትዕግሥት የሌለው ሰው ብስጩ፣ ነጭናጫ አልፎ ተርፎም ቁጡ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ባሕርያት ደግሞ በውስጣችን ውጥረት ስለሚፈጥሩ ጤንነታችንን ይጎዱታል። የአሜሪካ የሕክምና ማኅበር በቅርቡ ያወጣው አንድ ጥናት በግልጽ እንዳሳየው ትዕግሥት ማጣት ወጣቶችንም ጭምር ለደም ግፊት በሽታ ሊያጋልጥ ይችላል።

ትዕግሥት ማጣት ሌሎችም የጤና ችግሮች ያስከትላል። በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ትዕግሥት ማጣት ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረት ሊያጋልጥ ይችላል። ዘ ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው “ታግሠው መጠበቅ ከሚችሉ ሰዎች ይልቅ ትዕግሥት የሌላቸው ግለሰቦች ከመጠን በላይ የመወፈር አጋጣሚያቸው ሰፊ እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ደርሰውበታል።” በአንዳንድ አካባቢዎች በቅናሽ ዋጋ የሚቀርቡ ቶሎ የሚደርሱ ምግቦች በማንኛውም ጊዜ በቀላሉ ስለሚገኙ ትዕግሥት የሌላቸው ብዙ ሰዎች እነዚህን ምግቦች ለመመገብ ይፈተናሉ።

ዛሬ ነገ ማለት፦

በለንደን የሚገኘው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምርምር ማዕከል ያካሄደው አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ትዕግሥት የሌላቸው ሰዎች ዛሬ ነገ የማለት ሥር የሰደደ ችግር አለባቸው። እነዚህ ሰዎች ጊዜ የሚወስዱ ሥራዎችን ለሌላ ጊዜ የሚያስተላልፏቸው እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን ለመጨረስ ትዕግሥቱ ስለሌላቸው ይሆን? ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን፣ ዛሬ ነገ የማለት አባዜ በራሳቸውም ሆነ በኢኮኖሚው ላይ ከባድ ችግር ሊያስከትል ይችላል። በብሪታንያ የሚታተመው ዘ ቴሌግራፍ የተሰኘው ጋዜጣ እንደገለጸው ከሆነ ኤርኔስቶ ሩበን የተባሉት ተመራማሪ እንዲህ ብለዋል፦ “ዛሬ ነገ ማለት በሥራ ላይ ያለንን ምርታማነት በጣም ይነካል፤ እንዲሁም [ትዕግሥት የሌላቸው ሰዎች] የጽሑፍ ሥራን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ልማድ ስለሆነባቸው ሌሎች ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሣራ ሊዳረጉ ይችላሉ።”

ከልክ በላይ መጠጣትና ዓመፅ፦

ሳውዝ ዌልስ ኤኮ በተሰኘው የብሪታንያ ጋዜጣ መሠረት “ትዕግሥት የሌላቸው ሰዎች ሌሊት ላይ በመጠጥ ገፋፊነት በሚነሱ ግጭቶች ውስጥ የመግባት አጋጣሚያቸው ከፍ ያለ ነው።” በካርዲፍ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ተመራማሪዎች እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት በመቶዎች በሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች ላይ ጥናት ካካሄዱ በኋላ ነው። “ትዕግሥት የሌላቸው ሰዎች ከመጠን በላይ የመጠጣትና ዓመፅ የመፈጸም አጋጣሚያቸው ሰፊ” መሆኑን ጥናቱ ይፋ እንዳደረገ ኤኮ ገልጿል።

የተዛባ የማመዛዘን ችሎታ፦

በዋሽንግተን ዲሲ፣ ፒዩ በተሰኘው የምርምር ማዕከል ውስጥ የሚሠሩ ተንታኞች ትዕግሥት የሌላቸው ሰዎች “ብዙውን ጊዜ ያልታሰበባቸው የችኮላ ውሳኔዎችን እንደሚያደርጉ” ገልጸዋል። በሕንድ የባህራቲዳሳን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርና የማኅበራዊ ሥራ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ኢላንጎ ፖንሃስዋሚ ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። እኚህ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “ትዕግሥተኛ አለመሆን ዋጋ ያስከፍላችኋል። ትዕግሥት ማጣት ብዙውን ጊዜ መጥፎ ውሳኔ ወደ ማድረግ ስለሚመራ ገንዘባችሁንና ወዳጆቻችሁን ሊያሳጣችሁ፣ ሥቃይና መከራ ሊያመጣባችሁ ወይም ሌሎች ብዙ መዘዞችን ሊያስከትልባችሁ ይችላል።”

የገንዘብ ችግር፦

በዩናይትድ ስቴትስ ያለው የቦስተን ፌደራል ሪዘርቭ ባንክ የሚያሳትመው ሪሰርች ሪቪው የተባለ መጽሔት እንደገለጸው ትዕግሥት ማጣት “ከባድ ዕዳ ውስጥ ወደ መዘፈቅ” ሊያመራ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ትዕግሥተኛ ያልሆኑ አዲስ ተጋቢዎች የገንዘብ አቅማቸው ውስን ቢሆንም እንደተጋቡ የተሟላ ቤት እንዲኖራቸው ይፈልጉ ይሆናል። ስለዚህ ቤት፣ የቤት ዕቃ፣ መኪናና ሌላውንም ነገር ሁሉ በብድር ይገዛሉ። እንዲህ ማድረጋቸው በትዳራቸው ውስጥ ችግር ሊፈጥር ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ የአርከንሶ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንደተናገሩት “ዕዳ ያለባቸው አዲስ ተጋቢዎች፣ አነስተኛ ዕዳ ካለባቸው ወይም ምንም ዕዳ ከሌለባቸው ባልና ሚስቶች ጋር ሲነጻጸሩ እምብዛም ደስተኞች አይደሉም።”

በዩናይትድ ስቴትስ በቅርብ ለተከሰተው የኢኮኖሚ ድቀት መንስኤው ትዕግሥት ማጣት እንደሆነ አንዳንዶች ይናገራሉ። ፎርብዝ የተሰኘው ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን የሚዘግብ መጽሔት እንደሚከተለው ይላል፦ “በአሁኑ ጊዜ ላለው የኢኮኖሚ ሁኔታ አስተዋጽኦ ያደረገው ትዕግሥት ማጣትና ከልክ ያለፈ ስግብግብነት ነው። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተራ ሰዎች ትዕግሥት የለሽ መሆናቸው፣ ከአቅማቸው በላይ የሆኑና ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ንብረቶችን ማግኘት እንዲፈልጉ አድርጓቸዋል። በዚህም የተነሳ ለብዙ ዓመታት፣ እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታዎች እስከነጭራሹ ከፍለው መጨረስ የማይችሉትን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተበድረዋል።”

ወዳጆችን ማጣት፦

ትዕግሥት ማጣት ከሌሎች ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዳናደርግ እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። አንድ ሰው ጊዜ ወስዶ ጥሩ ጭውውት ለማድረግ ትዕግሥት ከሌለው የታሰበበት ሐሳብ መሰንዘር ሊያስቸግረው ይችላል። እንዲሁም ሌሎች ሐሳብ ሲሰጡ ሊበሳጭ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ሌሎች ለመናገር የፈለጉትን እስኪጨርሱ ለመጠበቅ ትዕግሥቱ የለውም። ሌሎች ሲናገሩ ለማዳመጥ ትዕግሥት ስለሌለው ጣልቃ እየገባ የጀመሩትን ዓረፍተ ነገር ለመጨረስ ሊሞክር ወይም ንግግራቸውን ቶሎ እንዲቋጩ ለማድረግ ሌሎች መንገዶችን ሊጠቀም ይችላል።

ትዕግሥት የሌለው ሰው ወዳጆቹን ሊያጣ ይችላል። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሱትና የአእምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ጄኒፈር ሀርትሽታይን እንዲህ ብለዋል፦ “ትዕግሥት አጥቶ ከሚቁነጠነጥ ወይም አሥር ጊዜ ሰዓቱን ከሚያይ ሰው ጋር መሆን ማን ይፈልጋል?” አዎን፣ ትዕግሥተኛ አለመሆን የሚወደድ ባሕርይ አይደለም። ወዳጆችህን ያሳጣሃል።

ትዕግሥት ማጣት የሚያስከትላቸው መጥፎ መዘዞች በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ብቻ አይደሉም። የሚቀጥለው ርዕስ ትዕግሥትን ማዳበርና ሁልጊዜ ይህን ባሕርይ ማሳየት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።