በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንቆቅልሽ የሆነው እንባ

እንቆቅልሽ የሆነው እንባ

ማልቀስ ከተወለድንበት ቀን ጀምሮ ከእኛ ጋር የሚኖር ነገር ነው። ሕፃን ሳለን ስሜታዊና አካላዊ ፍላጎቶቻችን እንዲሟሉልን የምንጠይቀው በማልቀስ ነው፤ በመሆኑም ለቅሶ “የድምፅ እትብት” ሊባል እንደሚችል አንድ ባለሙያ ገልጸዋል። ታዲያ እያደግን ስንሄድ በሌሎች መንገዶች ስሜታችንን መግለጽ ስንችል እንባችንን የምናፈስሰው ለምንድን ነው?

ከስሜት ጋር በተያያዘ እንባችንን የምናፈስስባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ስናዝን፣ ስንበሳጭ ወይም አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ሥቃይ ሲደርስብን ልናለቅስ እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ በጣም ስንደሰት፣ እፎይታ ሲሰማን ወይም ስኬት ስናገኝ ከስሜት ጋር ተያይዞ የሚመጣ እንባ እናነባለን፤ በዚህ ጊዜ ግን እንባችን የደስታ ነው። በተጨማሪም ማንባት ይጋባል። ማሪያ “ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ሰው ሲያለቅስ ካየሁ እኔም እንባዬን መቆጣጠር ያቅተኛል” ብላለች። በፊልም ላይ የተመለከትከው ወይም በመጽሐፍ ላይ ያነበብከው ምናባዊ ታሪክ አስለቅሶህ ይሆናል።

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ማልቀስ ከፍተኛ ኃይል ያለው ንግግር አልባ ቋንቋ ነው። የአዋቂዎች ለቅሶ (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ፣ የእንባን ያህል “በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገር ለመግለጽ የሚያስችሉ ሌሎች መንገዶች” እንደሌሉ ገልጿል። እንባ፣ ሰዎች አንድ እርምጃ እንዲወስዱ ያነሳሳል። ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኞቻችን የሐዘን እንባ አይተን ችላ ብለን ማለፍ አንችልም፤ ምክንያቱም ለቅሶው ግለሰቡ በሥቃይ ውስጥ መሆኑን ይጠቁመናል። በመሆኑም የሚያለቅሰውን ሰው ለማጽናናት ወይም ለመርዳት እንገፋፋለን።

አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ማልቀስ በውስጣችን ያለውን የታመቀ ስሜት እንዲወጣልን የሚያደርግ ጠቃሚ ዘዴ ስለሆነ እንባን አምቆ የመያዝ ልማድ ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ሌሎች ደግሞ ማልቀስ የሚያስገኘው አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ጥቅም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አልተረጋገጠም ብለው ይከራከራሉ። ያም ሆነ ይህ፣ 85 በመቶ የሚሆኑ ሴቶችና 73 በመቶ የሚሆኑ ወንዶች ካለቀሱ በኋላ ቀለል እንዳላቸው ጥናቶች አመልክተዋል። ኖኤሚ “ማልቀስ እንደሚያስፈልገኝ የሚሰማኝ ጊዜ አለ” ብላለች። “ከዚያም በረጅሙ ከተነፈስኩ በኋላ እውነታውን ይበልጥ አጥርቼ ማየት እችላለሁ።”

ጥናቶች እንደሚያሳዩት 85 በመቶ የሚሆኑ ሴቶችና 73 በመቶ የሚሆኑ ወንዶች ካለቀሱ በኋላ ቀለል ይላቸዋል

ይሁን እንጂ ይህ የእፎይታ ስሜት እንባ በማፍሰስ ብቻ የሚገኝ ላይሆን ይችላል። ሌሎች ለለቅሷችን የሚሰጡት ምላሽም በዚህ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ  ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰዎች እንባችንን አይተው ሲያጽናኑን ወይም ሲረዱን የእፎይታ ስሜት ይሰማናል። በምናለቅስበት ወቅት ተገቢውን ምላሽ ከሰዎች ካላገኘን የኃፍረትና የመገለል ስሜት ሊሰማን ይችላል።

ከለቅሶ ጋር በተያያዘ ብዙ እንቆቅልሽ የሆኑ ነገሮች እንዳሉ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አንድ የምናውቀው ነገር አለ፤ እንባን ማፍሰስ አምላክ ከሰጠን አስደናቂ የስሜት መግለጫዎች አንዱ ነው።