በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓይናማዋ እንስሳ

ዓይናማዋ እንስሳ

ብዙዎች ‘ቆንጅዬ ናት’ ይላሉ፤ አንዳንዶች ግን ‘እንግዳ ፍጥረት’ ብለው ይጠሯት ይሆናል። ቀጭን እግሮች፣ ለስላሳ ፀጉርና ትላልቅ ዓይኖች አሏት። ቁመቷ 12.5 ሴንቲ ሜትር ክብደቷ ደግሞ 114 ግራም ገደማ ነው። ለመሆኑ ይህች እንስሳ ምንድን ናት? ታርሲየር ትባላለች!

እስቲ በፊሊፒንስ ስለምትገኘው ታርሲየር አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት። ዓይኖቿ፣ ጆሮዎቿ፣ እጆቿ፣ እግሮቿ፣ ቅልጥሞቿና ጅራቷ ትልቅ በመሆናቸው ከሰውነቷ ጋር ተመጣጣኝ አይመስሉም። ሆኖም ይህችን ለየት ያለች ፍጥረት ቀረብ ብለን ስንመለከታት በአፈጣጠሯ ላይ የሚንጸባረቀውን አስደናቂ ንድፍ ማየት እንችላለን።

የመስማት ችሎታ፦ እንደ ወረቀት ስስ የሆኑት የታርሲየር ጆሮዎች መጠቅለልና መዘርጋት የሚችሉ ከመሆኑም ሌላ በጣም ዝቅተኛ ድምፅ ለመስማት ድምፁ ወደተሰማበት አቅጣጫ ይዞራሉ። ይህች እንስሳ ያላት ድንቅ የሆነ የመስማት ችሎታ እንደ ዱር ድመት ካሉ አዳኞች ለማምለጥ ብቻ ሳይሆን እሷ ራሷ የምታድናቸውን እንስሳት ለመፈለግም ይረዳታል። ከጨለመ በኋላ ጆሮዎቿ የእንጭራሪቶችን፣ የምስጦችን፣ የጥንዚዛዎችን፣ የወፎችንና የእንቁራሪቶችን ድምፅ በንቃት ይከታተላሉ። ከዚያም ድምፁን ወደሰማችበት አቅጣጫ ፊቷን አዙራ በእነዚያ ትላልቅ ዓይኖቿ ምግብ መፈለጓን ትያያዘዋለች።

የመጨበጥ ችሎታ፦ የታርሲየር እጆች ቀጫጭን ቅርንጫፎችን ለመጨበጥ ተስማሚ ሆነው የተሠሩ ናቸው። የጣቶቿ ጫፎች በጎማ ላይ እንዳሉ ጥርሶች ቆንጥጠው የሚይዙ ልዩ የሆኑ ተረተሮች አሏቸው። ይህች እንስሳ በምትተኛበት ጊዜም ጭምር የዛፍ ቅርንጫፍ ጨብጣ ትይዛለች። በረጅም ጅራቷ ላይ ከውስጥ በኩል ያሉት ተረተሮች ከእንቅልፏ እስክትነቃ ድረስ ባለችበት ቦታ ላይ እንድትቆይ ይረዷታል።

 እይታ፦ ከታርሲየር በቀር ከሰውነቱ ጋር ሲነጻጸር እንዲህ ያሉ ትላልቅ ዓይኖች ያሉት ሌላ አጥቢ እንስሳ የለም። እንዲያውም አንዱ ዓይኗ እንኳ ከአንጎሏ ይበልጣል! የታርሲየር ዓይኖች መሽከርከር አይችሉም፤ ከዚህ ይልቅ የሚያዩት ወደፊት ብቻ ነው። ታዲያ ይህ መሆኑ ጉዳት አለው? የለውም። ምክንያቱም ታርሲየር ለየት ያለ ችሎታ አላት፤ ዓይኖቿን ማንቀሳቀስ ሳያስፈልጋት አንገቷን በሁለቱም አቅጣጫ እስከ 180 ዲግሪ ድረስ ማዞር ትችላለች።

ቅልጥፍና፦ ታርሲየር ረጃጅም ቅልጥሞች ስላላት እስከ 6 ሜትር ድረስ መዝለል ትችላለች፤ ይህም ከቁመቷ 40 ጊዜ እጥፍ ይበልጣል! ይህች ትንሽ እንስሳ ምሽት ላይ ስታድን ዘላ በመነሳት ሰለባዋን እጇ ውስጥ ታስገባለች፤ እንዲህ የምታደርገው በፍጥነት በመሆኑ የምታድነው እንስሳ አያመልጣትም ሊባል ይችላል።

ታርሲየሮች አብዛኛውን ጊዜ በመካነ አራዊት ውስጥ በሕይወት መቀጠል አይችሉም፤ ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል በሕይወት ያሉ ነፍሳትን በልተው የማይጠግቡና ሰዎች እንዲቆጣጠሯቸው የማይፈልጉ መሆናቸው ይገኙበታል። ያም ሆኖ ይህች አስደናቂ እንስሳ የፊሊፒንስን ሕዝብ ቀልብ መሳቧን ቀጥላለች። በእርግጥም በደን ውስጥ የምትኖረው ዓይናማዋ ታርሲየር ሁሉ ነገሯ የሚገርም ነው።