በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ይጠቅማል?

ታማኝነት

ታማኝነት

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን።”—ዕብራውያን 13:4

የሚያስገኘው ጥቅም፦ አንዳንድ ሰዎች ይህ ሐሳብ ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በጣም ተሳስተዋል! ለትዳር ጓደኛ ታማኝ አለመሆን መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዛሬው ጊዜም ከባድ ጉዳት ያስከትላል።—ምሳሌ 6:34, 35

ጄሲ ባለትዳርና የልጆች አባት ሲሆን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በትዳራችን ውስጥ አንዳችን ለሌላው ታማኝ መሆናችን ከባለቤቴ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖረንና ቤተሰባችን ደስተኛ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። በእርግጥም መተማመን በትዳር ውስጥ በጣም አስፈላጊ ነው። ለትዳር ጓደኛ ታማኝ አለመሆን ግን ይህ የመተማመን ስሜት እንዲጠፋ ያደርጋል።” ከዚህም በተጨማሪ በልጆች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳድራል።

ሊጋያ * ትዳሯን አደጋ ላይ ጥላ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “መጥፎ ምግባር ካላቸው ሰዎች ጋር ጓደኝነት መሠረትኩ። በዚህም የተነሳ ወደ ምሽት ክበቦች መሄድ ጀመርኩ፤ እንዲሁም ምንዝር በመፈጸም ታማኝነቴን አጎደልኩ።” ታዲያ ይህ አኗኗሯ ደስታ አስገኝቶላታል? ከባለቤቷ ጋር ሁልጊዜ ይጨቃጨቁ የነበረ ሲሆን ደስታ አጣች። ሊጋያ እንዲህ ብላለች፦ “ምን ያህል አሳፋሪ ድርጊት ውስጥ እንደተዘፈቅኩ ሳስብ ወላጆቼ ‘መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል’ ይሉኝ የነበረው ትዝ አለኝ።”—1 ቆሮንቶስ 15:33

አክላም ሊጋያ እንዲህ ብላለች፦ “ነገሮች ከመባባሳቸው በፊት መጥፎ አካሄዴን አቁሜ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና የተማርኩትን በሚገባ ሥራ ላይ ለማዋል ወሰንኩ።” ውጤቱስ? ትዳሯ ከመፍረስ ዳነ፤ ባለቤቷም ከበፊቱ ይበልጥ በደግነትና በአክብሮት ይይዛት ጀመር። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን ለውጦታል፤ የቀድሞ አኗኗሬንና ጓደኛ ብዬ የያዝኳቸውን ሰዎች እርግፍ አድርጌ በመተዌ ፈጽሞ አልቆጭም።”

^ አን.6 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።