በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጥንቶቹ የዕብራይስጥ ፊደላት የተጻፈው የአምላክ ስም በእጅ በተገለበጡ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ውስጥ በብዛት ይገኛል

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የአምላክ ስም

የአምላክ ስም

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክን ጌታ፣ ፈጣሪ፣ አላህ ወይም አምላክ እንደሚሉት ባሉ አክብሮትን የሚያሳዩ የማዕረግ ስሞች ይጠሩታል። ይሁን እንጂ አምላክ የግል መጠሪያ ስም አለው። ታዲያ በዚህ ስም ልትጠቀምበት ይገባል?

የአምላክ ስም ማን ነው?

አንዳንዶች ምን ይላሉ?

 

ክርስቲያን ነን የሚሉ በርካታ ሰዎች የአምላክ ስም ኢየሱስ እንደሆነ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ አንድ ብቻ ስለሆነ እሱን ለመጥራት ልዩ ስም መጠቀም እንደማያስፈልግ ይሰማቸዋል። አምላክን በስሙ መጥራት ተገቢ አይደለም ብለው የሚከራከሩ ሰዎችም አሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 

ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ስም ኢየሱስ አይደለም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ሁሉን የሚችለው አምላክ አይደለም። እንዲያውም ኢየሱስ ልክ እንደ እሱ የአምላክ አገልጋይ የሆኑ ተከታዮቹን “አባት ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ሉቃስ 11:2) ኢየሱስ ራሱም ቢሆን “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” በማለት ጸልዮአል።—ዮሐንስ 12:28

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አምላክ “እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ . . . አልሰጥም” ብሏል። (ኢሳይያስ 42:8) “ይሖዋ” የሚለው የአማርኛ መጠሪያ የአምላክን ስም ከሚወክሉት የሐወሐ የሚሉት አራት የዕብራይስጥ ተነባቢ ፊደላት የተወሰደ ነው። ይህ ስም በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብለው በሚጠሩት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ 7000 ጊዜ ገደማ ተጠቅሶ ይገኛል። * ይሖዋ የሚለው ስም “አምላክ፣” “ሁሉን ቻይ” ወይም “ጌታ” እንደሚሉት ካሉ የማዕረግ ስሞች እንዲሁም አብርሃም፣ ሙሴ ወይም ዳዊት እንደሚሉት ካሉ የግለሰብ ስሞች ይበልጥ በብዛት ተጠቅሶ ይገኛል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ስሙን አክብሮት ባለው መንገድ እንዳንጠቀም የከለከለበት ቦታ አናገኝም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮች ስሙን በነፃነት ይጠቀሙበት እንደነበር ይጠቁማል። ለምሳሌ ለልጆቻቸው በሚያወጡት ስም ላይ የአምላክን ስም ያካትቱ ነበር፤ “አምላኬ ይሖዋ ነው” የሚል ትርጉም ያለውን ኤልያስ የሚለውን ስምና “ይሖዋ አስታውሷል” የሚል ትርጉም ያለውን ዘካርያስ የሚለውን ስም እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በተጨማሪም የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች በዕለት ተዕለት ጭውውታቸው የአምላክን ስም ይጠቀሙ ነበር።—ሩት 2:4

አምላክ በስሙ እንድንጠቀም ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ይሖዋን እንድናመሰግንና ስሙን እንድንጠራ’ ያበረታታናል። (መዝሙር 105:1) እንዲያውም አምላክ “በስሙ ላይ ለሚያሰላስሉ” ሰዎች ልዩ ሞገስ ያሳያል።—ሚልክያስ 3:16

“ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ይወቁ።”—መዝሙር 83:18

የአምላክ ስም ትርጉም ምንድን ነው?

አንዳንድ ምሁራን ይሖዋ የሚለው ስም በዕብራይስጥ “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም እንዳለው ያምናሉ። ይህ ትርጉም አምላክ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚሆንና ፍጥረታቱም እሱ የሚፈልገውን እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ይጠቁማል። እንዲህ ባለው ስም ሊጠራ የሚችለው ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ ብቻ ነው።

ይህን ማወቅህ ምን ለውጥ ያመጣል?

 

የአምላክን ስም ማወቅህ ስለ አምላክ ያለህን አመለካከት ይለውጠዋል። ወደ እሱ መቅረብ ይበልጥ ቀላል እንዲሆንልህ ያደርጋል። ደግሞስ ስሙን የማታውቀውን አካል እንዴት ልትቀርበው ትችላለህ? አምላክ ስሙን ላንተ መግለጡ በራሱ ወደ እሱ እንድትቀርብ እንደሚፈልግ ያሳያል።—ያዕቆብ 4:8

ይሖዋ የገባውን ቃል በመጠበቅ ምንጊዜም ከስሙ ትርጉም ጋር ተስማምቶ እንደሚገኝ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ስምህን የሚያውቁ በአንተ ይታመናሉ” የሚለው በዚህ ምክንያት ነው። (መዝሙር 9:10) ይሖዋ ከስሙ ትርጉም ጋር በተያያዘ የሚያደርጋቸው ነገሮች እንደ ታማኝ ፍቅር፣ ምሕረት፣ ርኅራኄና ፍትሕ ካሉት ባሕርያቱ የሚመነጩ ናቸው፤ ይህን እያወቅክ ስትሄድ በአምላክ ላይ እንዲህ ያለ እምነት ልታዳብር ትችላለህ። (ዘፀአት 34:5-7) በእርግጥም ይሖዋ ቃሉን ለመጠበቅ ሲል የሚወስዳቸው እርምጃዎች መቼም ቢሆን ከባሕርያቱ ጋር እንደማይቃረኑ ማወቅ የሚያጽናና ነው።

ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ በስም ማወቅ ትልቅ መብት ነው። የአምላክን ስም ማወቅህ ዛሬም ሆነ ወደፊት ብዙ በረከት ያስገኝልሃል። አምላክ “ስሜን ስለሚያውቅ እጠብቀዋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል።—መዝሙር 91:14

“የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”—ኢዩኤል 2:32

የአምላክ ስም በተለያዩ ቋንቋዎች

^ አን.9 ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የአምላክን ስም አውጥተው በዚያ ቦታ ላይ “ጌታ” ወይም “እግዚአብሔር” የሚሉትን የማዕረግ ስሞች ለየት ባለ የፊደል አጣጣል አስገብተዋል፤ ሌሎች ደግሞ የአምላክን ስም ያስገቡት በጥቂት ጥቅሶች ወይም የግርጌ ማሳታወሻዎች ላይ ብቻ ነው። ከዚህ በተለየ መልኩ አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የአምላክን ስም በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ አስገብቷል።