በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቴክኖሎጂ የሚያሳድረው ተጽዕኖ—​ከሌሎች ጋር ባለህ ወዳጅነት ላይ

ቴክኖሎጂ የሚያሳድረው ተጽዕኖ—​ከሌሎች ጋር ባለህ ወዳጅነት ላይ

የጽሑፍ መልእክት፣ ኢሜይል፣ ቪዲዮ ኮንፈረንስና ማኅበራዊ ሚዲያ የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በተለያዩ አህጉሮች የሚኖሩ ሰዎች እንኳ በቀላሉ እንዲገናኙ አስችለዋል። ለእነዚህ ሰዎች ቴክኖሎጂ ጥሩ አገልጋይ ሆኖላቸዋል።

ይሁንና በዋነኝነት በቴክኖሎጂ ውጤቶች አማካኝነት ከጓደኞቻቸው ጋር የሚገናኙ አንዳንድ ሰዎች የሚከተሉት አዝማሚያዎች ይታዩባቸዋል፦

  • የጓደኞቻቸውን ስሜት መረዳት ይከብዳቸዋል።

  • ከሌሎች የበለጠ የብቸኝነትና የባዶነት ስሜት ይሰማቸዋል።

  • በራሳቸው ላይ ብቻ ማተኮር ይቀናቸዋል።

ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

የሌሎችን ስሜት መረዳት

የሌሎችን ስሜት ለመረዳት ጊዜ ወስዶ ስለ እነሱ ማሰብ ያስፈልጋል፤ ይሁንና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚለጠፉት ነገሮች ብዙ ስለሆኑ እንዲሁም የጽሑፍ መልእክቶችን ማንበብ ወይም መላክ ሰፊ ጊዜ ስለሚወስድ እንዲህ ማድረግ ከባድ ሊሆንብን ይችላል።

የሚላኩልህ መልእክቶች በጣም ብዙ ከሆኑ የጓደኞችህን መልእክቶች አንብቦ መመለስ ሥራ ሊሆንብህ ይችላል። የመልእክት ሣጥንህን በማጽዳት ላይ ስታተኩር እርዳታ ለሚያስፈልገው ጓደኛህ ተገቢውን ምላሽ ሳትሰጥ ልትቀር ትችላለህ።

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተጠቅመህ ከጓደኞችህ ጋር መልእክት ስትላላክ የእነሱን ‘ስሜት እንደምትረዳ’ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?—1 ጴጥሮስ 3:8

የባዶነት ስሜት

አንድ ጥናት እንደጠቆመው ብዙ ሰዎች ታዋቂ የሆኑ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ሲቃኙ ከቆዩ በኋላ ከቀድሞው የባሰ መጥፎ ስሜት ይሰማቸዋል። ተመራማሪዎቹ፣ ሰዎች ሌሎች የለጠፏቸውን አዳዲስ ነገሮች ሲመለከቱ “እነሱ ምንም ጠቃሚ ነገር እንዳላከናወኑ ሊሰማቸው እንደሚችል” ገልጸዋል።

በተጨማሪም፣ ሰዎች አስደሳች ነገሮችን ሲያደርጉ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ሲመለከቱ የራሳቸውን ሕይወት ከእነሱ ሕይወት ጋር ማወዳደር ይጀምሩ ይሆናል። ይህ ደግሞ ሁሉም ሰው አስደሳች ጊዜ እያሳለፈ እንዳለ፣ የእነሱ ሕይወት ግን አሰልቺ እንደሆነ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል።

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ስትጠቀም ራስህን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ስለ ራስህ መጥፎ ስሜት እንዳያድርብህ ምን ሊረዳህ ይችላል?—ገላትያ 6:4

በራስ ላይ ማተኮር

አንዲት አስተማሪ፣ ከተማሪዎቿ መካከል አንዳንዶቹ ራስ ወዳዶች እንደሆኑና ከሁሉ በላይ የሚያሳስባቸው “የእኔ ደጋፊ ማን ነው?” የሚለው ጉዳይ እንደሆነ ተናግራለች። * እነዚህ ሰዎች የሚያተኩሩት ከጓደኞቻቸው በሚያገኙት ጥቅም ላይ ብቻ ነው። ጓደኞቻቸውን፣ ሲፈልጉ ተጠቅመው እንደሚዘጉት አፕሊኬሽን መመልከት ሊጀምሩ ይችላሉ።

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ኢንተርኔት ላይ የምትለጥፋቸው ነገሮች ከሌሎች ጋር የመፎካከር ወይም ከልክ በላይ በራስህ ላይ የማተኮር ዝንባሌ እንዳለህ ይጠቁማሉ?—ገላትያ 5:26

ምን ማድረግ ትችላለህ?

የቴክኖሎጂ አጠቃቀምህን ገምግም

ቴክኖሎጂ ጌታህ ሳይሆን አገልጋይህ ከሆነ ከጓደኞችህ ጋር እንድትገናኝ አልፎ ተርፎም ይበልጥ እንድትቀራረብ ይረዳሃል።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ፍቅር . . . የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።”—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5

ልትሠራባቸው የምትፈልጋቸውን ነጥቦች ለማስተዋል ሞክር፤ ወይም የራስህን ሐሳቦች ጻፍ።

  • የጽሑፍ መልእክት ወይም ኢሜይል ብቻ ከመላላክ ይልቅ በአካል ተገናኝቶ ለማውራት ጥረት ማድረግ

  • ከሌሎች ጋር ስትነጋገር ስልክህን ማራቅ (ወይም ድምፁን ማጥፋት)

  • ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመቃኘት የምታሳልፈውን ጊዜ መቀነስ

  • ጥሩ አድማጭ መሆን

  • ችግር ያጋጠመውን ጓደኛህን ለማነጋገር ጥረት ማድረግ

^ አን.17 ሪክሌሚንግ ኮንቨርሴሽን በተባለው መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰ።