በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መግቢያ

መግቢያ

ይህ መጽሐፍ እውነተኛ ታሪኮችን የያዘ ነው። ታሪኮቹ የተወሰዱት በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ከማይገኝለት መጽሐፍ ማለትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ታሪኮቹ አምላክ መፍጠር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ያለውን የዓለም ታሪክ ይተርኩላችኋል። ሌላው ቀርቶ አምላክ ወደፊት የሚፈጽማቸውን ተስፋዎች ይገልጻሉ።

ይህ መጽሐፍ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ የሆነ ሐሳብ ይሰጣችኋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተገለጹት ሰዎችና ስላደረጓቸው ነገሮች ይናገራል። በተጨማሪም አምላክ ለሰዎች የሰጠውን በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር ታላቅ ተስፋ ይገልጻል።

በዚህ መጽሐፍ ውስጥ 116 ታሪኮች አሉ። እነዚህ ታሪኮች በስምንት ክፍሎች ተከፍለዋል። በእያንዳንዱ ክፍል መጀመሪያ ላይ ያለው ገጽ በዚያ ክፍል ውስጥ የተካተቱትን ታሪኮች በአጭሩ ይናገራል። ታሪኮቹ በአፈጻጸማቸው ቅደም ተከተል የቀረቡ ናቸው። ይህም አንዳንድ ሁኔታዎች ከሌሎች ክስተቶች ጋር በተያያዘ በታሪክ ውስጥ በየትኛው ጊዜ ላይ እንደተፈጸሙ ለማወቅ ይረዳችኋል።

ታሪኮቹ በቀላል አማርኛ የቀረቡ ናቸው። ብዙዎቻችሁ ከፍ ከፍ ያላችሁት ልጆች ታሪኮቹን ራሳችሁ ልታነቧቸው ትችላላችሁ። ወላጆችም ለትንንሽ ልጆቻችሁ እነዚህን ታሪኮች ደግማችሁ ደጋግማችሁ ብታነቡላቸው በጣም ደስ እንደሚላቸው መገንዘብ ትችላላችሁ። ይህ መጽሐፍ የልጆችንም ሆነ የአዋቂዎችን ስሜት የሚስቡ ታሪኮች የያዘ ሆኖ ታገኙታላችሁ።

በእያንዳንዱ ታሪክ መጨረሻ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ታገኛላችሁ። ታሪኮቹ የተመሠረቱባቸውን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንድታነቡ እናበረታታችኋለን። ለእያንዳንዱ ታሪክ የተዘጋጁ የክለሳ ጥያቄዎች ከታሪክ 116 ቀጥሎ ይገኛሉ፤ አንድን ታሪክ አንብበህ ስትጨርስ እነዚህን ጥያቄዎች በመመልከት መልሶቹን ለማስታወስ ሞክር።