በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 1

አምላክ የተለያዩ ነገሮችን መፍጠር ጀመረ

አምላክ የተለያዩ ነገሮችን መፍጠር ጀመረ

ያሉን ጥሩ ነገሮች ሁሉ አምላክ የሠራቸው ናቸው። በቀን ብርሃን እንድትሰጠን ፀሐይን እንዲሁም በማታ መጠነኛ ብርሃን ማግኘት እንድንችል ጨረቃንና ከዋክብትን ሠራ። በተጨማሪም አምላክ ምድርን መኖሪያ እንድትሆነን አድርጎ አዘጋጃት።

ሆኖም አምላክ መጀመሪያ የሠራቸው ነገሮች ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብትና ምድር አይደሉም። በመጀመሪያ የፈጠረው እነማንን እንደሆነ ታውቃለህ? አምላክ በመጀመሪያ እሱን የመሰሉ ሕያዋን አካሎች ፈጠረ። አምላክን ማየት እንደማንችል ሁሉ እነዚህንም ሕያዋን አካሎች ማየት አንችልም። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን መላእክት ብሎ ይጠራቸዋል። አምላክ መላእክትን የፈጠረው አብረውት በሰማይ እንዲኖሩ ነው።

አምላክ በመጀመሪያ የፈጠረው መልአክ በጣም ለየት ያለ ነበር። ይህ መልአክ የአምላክ የመጀመሪያ ልጅ ነው፤ ከአባቱም ጋር አብሮ ሠርቷል። አምላክ ሌሎችን ነገሮች በሙሉ ሲሠራ ረድቶታል። አምላክ ፀሐይን፣ ጨረቃን፣ ከዋክብትንና ምድራችንን ሲሠራ ይረዳው ነበር።

በዚያን ጊዜ ምድር ምን ትመስል ነበር? በመጀመሪያ በምድር ላይ ማንም ሊኖር አይችልም ነበር። መሬትን ሙሉ በሙሉ ከሸፈነው አንድ ትልቅ ውቅያኖስ በስተቀር ምንም ነገር አልነበረም። ነገር ግን አምላክ ሰዎች በምድር ላይ እንዲኖሩ ፈለገ። ስለዚህ የተለያዩ ነገሮችን ለእኛ ማዘጋጀት ጀመረ። ያደረጋቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

በመጀመሪያ ምድር ብርሃን ያስፈልጋት ነበር። ስለዚህ አምላክ ከፀሐይ የሚወጣው ብርሃን መሬት ላይ እንዲያበራ አደረገ። በዚህ መንገድ ቀንና ሌሊት መፈራረቅ ጀመሩ። ቀጥሎም አምላክ መሬት ከውቅያኖሱ ውኃ ከፍ ብሎ እንዲወጣ አደረገ።

በመጀመሪያ በመሬት ላይ ምንም ነገር አልነበረም። መሬት ልክ ሥዕሉ ላይ የምታየውን ትመስል ነበር። አበቦች፣ ዛፎችም ሆኑ እንስሳት አልነበሩባትም። ሌላው ቀርቶ በውቅያኖሶቹ ውስጥ እንኳ አንድም ዓሣ አልነበረም። ምድር ለእንስሳትና ለሰዎች ተስማሚ መኖሪያ እንድትሆን ለማድረግ አምላክ ብዙ ሥራ ይቀረው ነበር