በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 4

መኖሪያቸውን ያጡት ለምንድን ነው?

መኖሪያቸውን ያጡት ለምንድን ነው?

አሁን ምን እየተፈጸመ እንዳለ ተመልከት። አዳምና ሔዋን ውብ ከሆነችው የኤደን የአትክልት ስፍራ እየተባረሩ ነው። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?

አንድ በጣም መጥፎ የሆነ ድርጊት ስለ ፈጸሙ ነው። በመሆኑም ይሖዋ እየቀጣቸው ነው። አዳምና ሔዋን የፈጸሙት መጥፎ ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?

አምላክ አታድርጉ ብሎ የከለከላቸውን ነገር አደረጉ። አምላክ በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኙት ዛፎች መመገብ እንደሚችሉ ነገራቸው። ነገር ግን ከአንዱ የዛፍ ፍሬ እንዳይበሉና ከእርሱ ከበሉ እንደሚሞቱ ነገራቸው። ይህ ዛፍ የእሱ የግሉ ንብረት ነበር። የአንድን ሰው ንብረት መውሰድ ደግሞ ትክክል እንዳልሆነ እናውቃለን፤ አናውቅም እንዴ? ታዲያ ምን ሆነ?

ከዕለታት አንድ ቀን ሔዋን በአትክልት ስፍራው ውስጥ ብቻዋን በነበረችበት ጊዜ አንድ እባብ መጥቶ አነጋገራት። እስቲ አስበው! አምላክ እንዳይበሉ የከለከላቸውን ዛፍ ፍሬ እንድትበላ ነገራት። ይሖዋ እባቦችን ሲፈጥር መናገር እንዲችሉ አድርጎ አልፈጠራቸውም። እንግዲያው እባቡን እንዲናገር ያደረገው ሌላ አካል ነበር ማለት ነው። እርሱ ማን ነው?

አዳም አልነበረም። እንግዲያው ይሖዋ ምድርን ከመፍጠሩ ከረጅም ዘመን በፊት ከፈጠራቸው ሕያዋን አካላት አንዱ መሆን አለበት። እነዚህ ሕያዋን አካላት መላእክት ናቸው። እነርሱን ማየት አንችልም። ከእነዚህ መላእክት አንዱ በጣም ኩራተኛ ሆነ። እንደ አምላክ ገዥ መሆን አለብኝ ብሎ ማሰብ ጀመረ። በተጨማሪም ሰዎች ይሖዋን ከመታዘዝ ይልቅ እርሱን እንዲታዘዙ ፈለገ። እባቡን እንዲናገር ያደረገው መልአክ እርሱ ነበር።

ይህ መልአክ ሔዋንን ማታለል ችሏል። ፍሬውን ከበላች ልክ እንደ አምላክ ለመሆን እንደምትችል ሲነግራት አመነችው። ስለዚህ ከፍሬው በላች፤ አዳምም በላ። አዳምና ሔዋን አምላክን ሳይታዘዙ ቀሩ፤ መኖሪያቸው የሆነውን ውቡን የአትክልት ስፍራ ያጡበትም ምክንያት ይኸው ነው።

ይሁን እንጂ አምላክ አንድ ቀን መላዋ ምድር እንደዚያች የኤደን የአትክልት ስፍራ ውብ እንድትሆን ያደርጋል። ምድርን ውብ የአትክልት ቦታ በማድረጉ ሥራ እንዴት ልትካፈል እንደምትችል ወደፊት እንማራለን። አሁን ግን አዳምና ሔዋን ምን እንደደረሰባቸው እንመልከት