በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 6

አንድ ጥሩ ልጅና አንድ መጥፎ ልጅ

አንድ ጥሩ ልጅና አንድ መጥፎ ልጅ

ቃየንንና አቤልን ተመልከት። ሁለቱም አድገዋል። ቃየን ገበሬ ሆነ። ጥራ ጥሬና ፍራፍሬ እንዲሁም አትክልቶችን ያመርት ነበር።

አቤል በግ ጠባቂ ሆነ። ግልገሎችን መንከባከብ ይወድ ነበር። ግልገሎቹ አደጉና ትልልቅ በጎች ሆኑ። ስለዚህ ብዙም ሳይቆይ አቤል የሚጠብቃቸው በጎች ትልቅ መንጋ ሆኑ።

ከዕለታት አንድ ቀን ቃየንና አቤል ለአምላክ ስጦታ አቀረቡ። ቃየን ካመረተው እህል ለአምላክ ስጦታ አቀረበ። አቤል ደግሞ ካሉት በጎች ሁሉ የተሻለውን ምርጥ በግ አቀረበ። ይሖዋ በአቤልና በስጦታው ተደሰተ። ይሁን እንጂ በቃየንና በስጦታው አልተደሰተም። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?

የአቤል ስጦታ ከቃየን ስጦታ የተሻለ ስለሆነ ብቻ አልነበረም። አቤል ጥሩ ሰው ስለ ነበር ነው። ይሖዋንና ወንድሙን ይወድ ነበር። ቃየን ግን ክፉ ነበር። ወንድሙን አይወደውም ነበር።

ስለዚህ አምላክ ቃየን አስተሳሰቡን እንዲለውጥ ነገረው። ቃየን ግን ምክሩን አልተቀበለም። አምላክ አቤልን አብልጦ ስለወደደው ቃየን በኃይል ተናደደ። ስለዚህ ቃየን አቤልን ‘ወደ ሜዳ እንሂድ አለው።’ ወደ ሜዳ ከሄዱ በኋላ ብቻቸውን ሲሆኑ ቃየን ወንድሙን አቤልን መታው። በኃይል መትቶት ስለ ነበረ ሞተ። ቃየን ይህን ማድረጉ መጥፎ አልነበረምን?

ምንም እንኳን አቤል ቢሞትም አምላክ አሁንም ያስታውሰዋል። አቤል ጥሩ ሰው ነበር። ይሖዋ ደግሞ እንደርሱ ያሉትን ጥሩ ሰዎች አይረሳም። ስለዚህ ይሖዋ አምላክ አንድ ቀን አቤልን እንደገና በሕይወት እንዲኖር ያደርገዋል። በዚያ ጊዜ አቤል የግድ እንደገና መሞት አያስፈልገውም። በዚህ ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ይችላል። በዚያ ጊዜ እንደ አቤል ከመሰሉ ሰዎች ጋር መተዋወቅ ደስ አያሰኝም?

ይሁን እንጂ አምላክ እንደ ቃየን በመሳሰሉት ሰዎች አይደሰትም። ስለዚህ ቃየን ወንድሙን ከገደለ በኋላ ከቀሩት ቤተሰቦቹ ተለይቶ ወደ ሩቅ ቦታ እንዲሰደድ በማድረግ አምላክ ቀጥቶታል። ቃየን የነበረበትን ቦታ ለቅቆ በሌላ ቦታ ለመኖር ሲሄድ ከእህቶቹ አንዷን ይዞ ሄደ። እርሷም ሚስቱ ሆነች።

ከጊዜ በኋላ ቃየንና ሚስቱ ልጆችን መውለድ ጀመሩ። ሌሎቹ የአዳምና የሔዋን ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተጋቡና ልጆችን ወለዱ። ብዙም ሳይቆይ ሰዎች በምድር ላይ እየበዙ ሄዱ። እስቲ የአንዳንዶቹን ታሪክ እንመልከት