በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 7

ደፋር ሰው

ደፋር ሰው

ሰዎች በምድር ላይ እየበዙ ሲሄዱ አብዛኛዎቹ እንደ ቃየን መጥፎ ነገሮችን ያደርጉ ነበር። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሰዎች የተለየ አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው ሄኖክ ይባላል። ሄኖክ ደፋር ሰው ነበር። በዙሪያው የነበሩት ሰዎች ሁሉ በጣም መጥፎ የሆኑ ነገሮችን ይፈጽሙ ነበር። ያም ሆኖ ሄኖክ አምላክን ከማገልገል ወደ ኋላ አላለም።

በዚያ ጊዜ የነበሩት ሰዎች ብዙ መጥፎ ነገሮችን ይፈጽሙ የነበረው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? እስቲ ቆም በልና አስብ፤ አዳምና ሔዋን አምላክን እንዳይታዘዙና አምላክ አትብሉ ብሎ ከከለከላቸው ፍሬ እንዲበሉ ያደረጋቸው ማን ነበር? አዎ፣ አንድ ክፉ መልአክ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ክፉ መልአክ ሰይጣን ብሎ ይጠራዋል። እርሱ ሁሉም ሰው ክፉ እንዲሆን ለማድረግ በመጣር ላይ ይገኛል።

ይሖዋ አምላክ ከዕለታት አንድ ቀን ሰዎቹ መስማት የማይፈልጉትን አንድ ነገር እንዲነግራቸው ሄኖክን ላከው። መልእክቱም ‘አንድ ቀን አምላክ ክፉ ሰዎችን በሙሉ እንደሚያጠፋቸው’ የሚገልጽ ነበር። ሰዎቹ ይህን መስማታቸው ሳያናድዳቸው አልቀረም። ምናልባትም ሄኖክን ለመግደል ሞክረው ይሆናል። ስለዚህ ሄኖክ አምላክ ስለሚያደርገው ነገር ለሰዎቹ ለመንገር በጣም ደፋር መሆን አስፈልጎት ነበር።

ሄኖክ በእነዚህ ክፉ ሰዎች መካከል ለረጅም ጊዜ እንዲኖር አምላክ አልፈቀደም። ሄኖክ የኖረው 365 ዓመት ብቻ ነበር። “365 ዓመት ብቻ” የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በዚያን ጊዜ የነበሩ ሰዎች በእኛ ዘመን ካሉት ሰዎች ይበልጥ ጠንካራ ስለ ነበሩ ከእኛ የበለጠ እድሜ ነበራቸው። እንዲያውም የሄኖክ ልጅ ማቱሳላ 969 ዓመት ኖሯል!

ሄኖክ ከሞተም በኋላ ሰዎቹ ይበልጥ ክፉዎች እየሆኑ ሄዱ። ‘የሚያስቡት ነገር ሁሉ መጥፎ እንደነበርና ምድርም በዓመፅ እንደተሞላች’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።

በዚያ ዘመን በምድር ላይ ይህን ያህል አሳሳቢ ችግሮች ሊስፋፉ የቻሉበት አንዱ ምክንያት ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ሰይጣን ሰዎች መጥፎ ነገር እንዲያደርጉ የሚገፋፋ አዲስ ዘዴ ቀይሶ ስለነበረ ነው። ቀጥለን ስለዚህ ነገር እንማራለን