በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 9

ኖኅ መርከብ ሠራ

ኖኅ መርከብ ሠራ

ኖኅ አንዲት ሚስትና ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት። የልጆቹም ስም ሴም፣ ካምና ያፌት ነበር። እነዚህ ወንዶች ልጆች እያንዳንዳቸው ሚስት ነበራቸው። ስለዚህ በኖኅ ቤተሰብ ውስጥ ስምንት ሰዎች ነበሩ።

አምላክ አንድ ያልተለመደ ነገር እንዲያደርግ ኖኅን አዘዘው። አንድ ትልቅ መርከብ ሥራ አለው። ይህ መርከብ ትልቅና ረጅም ሣጥን ይመስል ነበር። ‘መርከቡ ሦስት ፎቅ ያለው ይሁን፤ በውስጡም የተለያዩ ክፍሎችን ሥራ’ በማለት አምላክ ኖኅን አዘዘው። እነዚህ ክፍሎች ለኖኅና ለቤተሰቡ፣ ለእንስሶቹ እንዲሁም ሁሉም የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ለማከማቸት የሚያገለግሉ ነበሩ።

በተጨማሪም አምላክ መርከቡን ምንም ውኃ እንዳያስገባ አድርጎ እንዲሠራው ለኖኅ ነገረው። አምላክ ‘ታላቅ የጥፋት ውኃ አምጥቼ ዓለምን በሙሉ አጠፋለሁ። መርከቡ ውስጥ ያልገባ ሰው ሁሉ ይሞታል’ ሲል ተናገረ።

ኖኅና ልጆቹ ይሖዋን በመታዘዝ መርከቡን መሥራት ጀመሩ። ሌሎቹ ሰዎች ግን ይስቁበት ነበር። መጥፎ ድርጊት መፈጸማቸውን ቀጠሉ። አምላክ ለማድረግ ያሰበውን ነገር ኖኅ ሲነግራቸው ያመነው ሰው አልነበረም።

መርከቡ በጣም ትልቅ ስለ ነበረ እርሱን ለመሥራት ብዙ ጊዜ ወሰደ። በመጨረሻ ከብዙ ዓመታት በኋላ ተሠርቶ አለቀ። ይህ ከሆነ በኋላ ኖኅ እንስሶቹን ወደ መርከቡ እንዲያስገባ አምላክ አዘዘው። ከተወሰኑ ዓይነት እንስሳት ወንድና ሴት እያደረገ ሁለት ሁለት እንዲያስገባ ነገረው። ይሁን እንጂ ከሌሎች ዓይነት እንስሳት ደግሞ ሰባት ሰባት እንዲያስገባ ነገረው። በተጨማሪም ሁሉንም ዓይነት ወፎች ወደ መርከቡ እንዲያስገባ አዘዘው። ኖኅ ልክ አምላክ እንዳለው አደረገ።

ከዚህ በኋላ ኖኅና ቤተሰቡም ወደ መርከቡ ገቡ። ከዚያም አምላክ በሩን ዘጋው። ኖኅና ቤተሰቡ መርከቡ ውስጥ እንዳሉ የሚሆነውን ነገር ይጠባበቁ ጀመር። እስቲ አንተም ከእነርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ ሆነህ አብረህ በመጠባበቅ ላይ እንዳለህ አድርገህ አስብ። በእርግጥ አምላክ እንዳለው የጥፋት ውኃ ይመጣ ይሆን?