በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 12

ሰዎች አንድ ትልቅ ግንብ ሠሩ

ሰዎች አንድ ትልቅ ግንብ ሠሩ

ብዙ ዓመታት አለፉ። የኖኅ ልጆች ብዙ ልጆች ወለዱ። የእነርሱ ልጆች ደግሞ አደጉና ሌሎች ልጆች ወለዱ። ብዙም ሳይቆይ በምድር ላይ የሚኖሩት ሰዎች ብዙ ሆኑ።

ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ከኖኅ የልጅ ልጅ የተወለደ ናምሩድ የተባለ ሰው ነበር። እንስሳትን የሚያድንና ሰዎችን የሚገድል ክፉ ሰው ነበር። በተጨማሪም ናምሩድ ሌሎቹን ሰዎች ለመግዛት ራሱን ንጉሥ ያደረገ ሰው ነው። አምላክ ናምሩድን አይወደውም ነበር።

በዚያ ጊዜ ሰዎች ሁሉ አንድ ቋንቋ ይናገሩ ነበር። ናምሩድ እነዚህን ሰዎች ለመግዛት እንዲችል ሁሉንም አንድ ላይ ለማሰባሰብ ፈለገ። ምን እንዳደረገ ታውቃለህ? ሰዎቹ አንዲት ከተማና በከተማይቱም ውስጥ አንድ ትልቅ ግንብ እንዲሠሩ አዘዛቸው። እነዚህ ሰዎች ጡብ ሲሠሩ ሥዕሉ ላይ ተመልከት።

ይሖዋ አምላክ እነዚህ ሰዎች ይህን ግንብ በመሥራታቸው አልተደሰተም። አምላክ ሰዎቹ ያንን ቦታ ጥለው እንዲሄዱና በምድር ሁሉ ላይ ተበታትነው እንዲኖሩ ይፈልግ ነበር። ሰዎቹ ግን እንዲህ አሉ:- ‘ኑ! ከተማና ሰማይ የሚደርስ ረጅም ግንብ እንሥራ። ከዚያ በኋላ የታወቅን እንሆናለን!’ ሰዎቹ ለአምላክ ሳይሆን ለራሳቸው ክብር ለማግኘት ፈለጉ።

ስለዚህ አምላክ ግንቡን መገንባታቸውን እንዲያቆሙ አደረገ። ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ? አንድ ቋንቋ ይናገሩ የነበሩት ሰዎች ድንገት የተለያየ ቋንቋ እንዲናገሩ አደረጋቸው። ከዚያ በኋላ ግንቡን ይገነቡ የነበሩት ሰዎች እርስ በርሳቸው ሊግባቡ አልቻሉም። ከተማቸው ባቤል ወይም ባቢሎን ተብላ የተጠራችው በዚህ ምክንያት ነው፤ ትርጓሜውም “ዝብርቅ” ማለት ነው።

በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ባቤልን እየለቀቁ መሄድ ጀመሩ። አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በቡድን በቡድን እየሆኑ አንድ ላይ ለመኖር ወደ ሌሎች የምድር ክፍሎች ተበተኑ።