በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 16

ይስሐቅ ጥሩ ሚስት አገኘ

ይስሐቅ ጥሩ ሚስት አገኘ

እዚህ ሥዕል ላይ ያለችው ሴት ማን እንደሆነች ታውቃለህ? ርብቃ ትባላለች። ወደ ይስሐቅ እየሄደች ነው። ርብቃ የእሱ ሚስት ልትሆን ነው። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

የይስሐቅ አባት የሆነው አብርሃም ልጁ ጥሩ ሚስት እንዲያገባ ፈለገ። ይስሐቅ በከነዓን ምድር ከነበሩት ሴቶች መካከል እንዲያገባ አልፈለገም፤ ምክንያቱም በዚያ የነበሩት ሰዎች የሐሰት አማልክትን የሚያመልኩ ነበሩ። ስለዚህ አብርሃም አገልጋዩን ጠራውና ‘ዘመዶቼ ወደሚኖሩበት ወደ ካራን ሄደህ ለልጄ ለይስሐቅ ሚስት አምጣለት’ አለው።

ወዲያውኑ የአብርሃም አገልጋይ አሥር ግመሎች ወሰደና ረጅሙን ጉዞ ተጓዘ። የአብርሃም ዘመዶች ወደሚኖሩበት ቦታ አቅራቢያ ሲደርስ በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ቆመ። ቀኑ ሊመሽ ተቃርቦ ነበር፤ የከተማው ሴቶችም ከጉድጓዱ ውኃ ለመቅዳት የሚመጡት በዚህ ጊዜ ነበር። ስለዚህ የአብርሃም አገልጋይ ‘እኔንም ሆነ ግመሎቹን ውኃ የምታጠጣዋ ሴት አንተ ለይስሐቅ የመረጥክለት ሚስት ትሁን’ በማለት ወደ ይሖዋ ጸለየ።

ብዙም ሳይቆይ ርብቃ ውኃ ለመቅዳት መጣች። አገልጋዩ ውኃ እንድታጠጣው ሲጠይቃት አጠጣችው። ከዚያም የተጠሙት ግመሎች እስኪረኩ ድረስ ውኃ እየቀዳች አጠጣቻቸው። ግመሎች በጣም ብዙ ውኃ ስለሚጠጡ ይህን ማድረጉ ከባድ ሥራ ነበር።

ርብቃ ይህን አድርጋ ስትጨርስ የአብርሃም አገልጋይ የአባቷን ስም እንድትነግረው ጠየቃት። በተጨማሪም እቤታቸው ማደር ይችል እንደሆነ ጠየቃት። ርብቃም ‘አባቴ ባቱኤል ይባላል፤ እኛ ጋር ማደር የምትችልበት ቦታም አለ’ አለችው። ባቱኤል የአብርሃም ወንድም የናኮር ልጅ እንደሆነ የአብርሃም አገልጋይ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ከአብርሃም ዘመዶች ጋር ስላገናኘው ተንበርክኮ ይሖዋን አመሰገነ።

በዚያን ዕለት ማታ የአብርሃም አገልጋይ ወደዚያ ቦታ የመጣበትን ምክንያት ለባቱኤልና ለርብቃ ወንድም ለላባ ነገራቸው። ሁለቱም በነገሩ በመስማማት ርብቃ አብራው ሄዳ ይስሐቅን ልታገባው እንደምትችል ነገሩት። ርብቃስ ስትጠየቅ ምን አለች? ‘እሄዳለሁ’ ስትል መለሰች፤ መሄድ ፈልጋ ነበር። ስለዚህ በሚቀጥለው ቀን ግመሎቹ ላይ ተቀመጡና ወደ ከነዓን ምድር ለመመለስ ረጅሙን መንገድ መጓዝ ጀመሩ።

ወደ ከነዓን ምድር ሲደርሱ መሽቶ ነበር። ርብቃ አንድ ሰው በሜዳው ላይ ሲሄድ ተመለከተች። ያየችው ሰው ይስሐቅ ነበር። ይስሐቅ ርብቃን ሲያይ በጣም ተደሰተ። እናቱ ሣራ ከሞተች ገና ሦስት ዓመቷ ስለ ነበር የተሰማው ሐዘን ከልቡ አልወጣም ነበር። አሁን ግን ይስሐቅ ርብቃን በጣም ስለ ወደዳት እንደገና ደስተኛ ሆነ።