በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 33

ቀይ ባሕርን መሻገር

ቀይ ባሕርን መሻገር

ምን እየተፈጸመ እንዳለ ተመልከት! በቀይ ባሕር ላይ በትሩን ሰንዝሮ የሚታየው ሙሴ ነው። በአንደኛው ወገን ከእሱ ጋር በደህና ሁኔታ ላይ የሚገኙት ሰዎች እስራኤላውያን ናቸው። ይሁን እንጂ ፈርዖንና ሠራዊቱ በሙሉ ባሕሩ ውስጥ እየሰጠሙ ነው። ይህ ሁኔታ ሊደርስ የቻለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ቀደም ሲል እንደተማርነው አምላክ አሥረኛውን መቅሰፍት በግብፃውያን ላይ ካመጣ በኋላ ፈርዖን እስራኤላውያን ግብፅን ለቀው እንዲወጡ ነግሯቸው ነበር። ወደ 600, 000 የሚጠጉ እስራኤላውያን ወንዶች እንዲሁም ብዙ ሴቶችና ልጆች ግብፅን ለቀው ወጡ። በተጨማሪም በይሖዋ ያመኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሌሎች ሰዎች ከእስራኤላውያን ጋር አብረው ወጡ። ሁሉም በጎቻቸውንና ፍየሎቻቸውን እንዲሁም ከብቶቻቸውን ይዘው ሄዱ።

እስራኤላውያን ከግብፅ ከመውጣታቸው በፊት ግብፃውያንን ልብሶችንና ከወርቅና ከብር የተሠሩ ነገሮችን እንዲሰጧቸው ጠይቀዋቸው ነበር። ግብፃውያን በእነርሱ ላይ በደረሰው የመጨረሻው መቅሰፍት የተነሳ ከፍተኛ ፍርሃት አድሮባቸው ነበር። ስለዚህ እስራኤላውያን የጠየቋቸውን ነገር ሁሉ ሰጧቸው።

ከጥቂት ቀናት በኋላ እስራኤላውያን ቀይ ባሕር አጠገብ ደረሱ። በዚያ ቦታም ዕረፍት አደረጉ። በዚህ ወቅት ፈርዖንና አገልጋዮቹ እስራኤላውያንን በመልቀቃቸው በጣም ተበሳጩ። ‘እንዴት ባሪያዎቻችንን እንለቃለን?’ በማለት ተናገሩ።

ስለዚህ ፈርዖን እንደገና ሐሳቡን ቀየረ። ወዲያውኑ የጦር ሰረገሎቹንና ሠራዊቱን አዘጋጀ። ከዚያም 600 ምርጥ ሰረገሎችና ሌሎቹንም የግብፅ ሰረገሎች በሙሉ ይዞ እስራኤላውያንን ማሳደድ ጀመረ።

እስራኤላውያን ፈርዖንና ሠራዊቱ እየተከተሏቸው መሆኑን ሲመለከቱ በጣም ፈሩ። ምንም ማምለጫ መንገድ አልነበረም። ከፊታቸው ቀይ ባሕር አለ፤ ከኋላቸው ደግሞ ግብፃውያን እየመጡ ነው። ቢሆንም ይሖዋ በሕዝቡና በግብፃውያን መካከል ደመና አደረገ። በዚህም የተነሳ ግብፃውያን እስራኤላውያንን ማየት ስላልቻሉ ሊያጠቋቸው አልቻሉም።

ከዚያም ይሖዋ ሙሴ በትሩን በቀይ ባሕር ላይ እንዲሰነዝር ነገረው። ሙሴ በትሩን በባሕሩ ላይ ሲሰነዝር ይሖዋ ኃይለኛ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ። የባሕሩ ውኃ ተከፈለና በሁለቱም ወገን ውኃው ቀጥ ብሎ ቆመ።

ከዚያም እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በደረቅ መሬት ላይ መጓዝ ጀመሩ። በሚልዮን የሚቆጠሩት ሰዎች ከያዙአቸው እንስሶች ጋር በሌላኛው ወገን ወዳለው ቦታ በባሕሩ ውስጥ ያለ ምንም ችግር ለመሻገር በርከት ያሉ ሰዓቶች ወስዶባቸዋል። በመጨረሻም ግብፃውያን እንደገና እስራኤላውያንን ማየት ቻሉ። ባሪያዎቻቸው እያመለጧቸው ነበር! በመሆኑም ወዲያውኑ እነርሱን ተከትለው ወደ ባሕሩ ገቡ።

እነርሱን ተከትለው ወደ ባሕሩ ሲገቡ አምላክ የሰረገሎቻቸውን ጎማዎች አወላለቃቸው። ግብፃውያን በጣም ፈሩ፤ ‘ይሖዋ ለእስራኤላውያን እየተዋጋላቸው ነው። ከዚህ ቦታ እንውጣ!’ እያሉ መጮኽ ጀመሩ። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ የሚችሉበት ጊዜ አልፎ ነበር።

ሥዕሉ ላይ እንደተመለከትከው ይሖዋ ሙሴን በትርህን በቀይ ባሕር ላይ ሰንዝር ያለው በዚህ ጊዜ ነበር። ሙሴ በትሩን በባሕሩ ላይ ሲሰነዝር እንደ ግድግዳ ቆሞ የነበረው ውኃ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰና ግብፃውያንንና ሰረገሎቻቸውን ዋጣቸው። ሠራዊቱ በሙሉ እስራኤላውያንን ተከትሎ ባሕሩ ውስጥ ገብቶ ነበር። በሕይወት ተርፎ ከባሕሩ ውስጥ የወጣ አንድም ግብፃዊ አልነበረም!

የአምላክ ሕዝቦች በመዳናቸው ምንኛ ተደስተው ይሆን! ወንዶቹ ‘ይሖዋ ታላቅ ድል ተቀዳጅቷል። ፈረሶቹንና ፈረሰኛዎቹን ባሕር ውስጥ ጥሏል’ በማለት የምስጋና መዝሙር ዘመሩ። የሙሴ እህት ሚርያም ከበሮዋን ይዛ ስትዘፍን ሴቶቹ በሙሉ ከበሮቻቸውን ይዘው አብረዋት መዝፈን ጀመሩ። ልክ እንደ ወንዶቹ ‘ይሖዋ ታላቅ ድል ተቀዳጅቷል። ፈረሶቹንና ፈረሰኞቹን በባሕር ውስጥ ጥሏል’ እያሉ በመዘመር በደስታ ጨፈሩ።