በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 35

ይሖዋ ሕጎቹን ሰጠ

ይሖዋ ሕጎቹን ሰጠ

እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ ወደ ሲና ተራራ መጡ፤ ይህ ተራራ ኮሬብ ተብሎም ይጠራል። ይሖዋ በእሳት ተያይዞ ከነበረው ቁጥቋጦ ውስጥ ሙሴን ያነጋገረው በዚህ ቦታ ነበር። ሕዝቡ በዚህ ቦታ ሰፍረው ለተወሰነ ጊዜ ቆይተዋል።

ሕዝቡ ታች ሆነው ሲጠባበቁ ሙሴ ወደ ተራራው ወጣ። ሙሴ ወደ ተራራው ጫፍ ከወጣ በኋላ ይሖዋ እስራኤላውያን እንዲታዘዙትና ለእርሱ የተለዩ ሕዝብ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ ነገረው። ሙሴ ከተራራው ሲወርድ ይሖዋ ያለውን ለእስራኤላውያን ነገራቸው። ሕዝቡም የይሖዋ ሕዝብ መሆን ስለፈለጉ ይሖዋን እንታዘዛለን አሉ።

በዚህ ጊዜ ይሖዋ አንድ ልዩ ነገር ፈጸመ። የተራራው ጫፍ እንዲጨስና ኃይለኛ የነጎድጓድ ድምፅ እንዲሰማ አደረገ። ሕዝቡንም ‘ከግብፅ ያወጣኋችሁ አምላካችሁ ይሖዋ እኔ ነኝ’ አላቸው። ከዚያም ‘ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክትን አታምልኩ’ ሲል አዘዛቸው።

አምላክ ለእስራኤላውያን ዘጠኝ ተጨማሪ ትእዛዛት ወይም ሕጎች ሰጣቸው። ሕዝቡ በጣም ፈሩ። ሙሴን ‘አምላክ ካነጋገረን ልንሞት እንችላለን፤ ስለዚህ አንተ ብትነግረን ይሻላል’ አሉት።

ከዚያ በኋላ ይሖዋ ሙሴን ‘እኔ ወዳለሁበት ወደ ተራራው ውጣ። ለሕዝቡ ያወጣኋቸውን ሕጎች የጻፍኩባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እሰጥሃለሁ’ አለው። ስለዚህ ሙሴ እንደገና ወደ ተራራው ወጣ። በተራራውም ላይ 40 ቀንና ሌሊት ቆየ።

አምላክ ለሕዝቡ በጣም ብዙ ሕጎች አውጥቶ ነበር። ሙሴ እነዚህን ሕጎች ጻፋቸው። በተጨማሪም አምላክ ለሙሴ ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች ሰጠው። አምላክ ለጠቅላላው ሕዝብ የተናገራቸውን 10 ሕጎች ራሱ በጽላቶቹ ላይ ጽፏቸው ነበር። እነዚህ ሕጎች አሥርቱ ትእዛዛት ተብለው ይጠራሉ።

አሥርቱ ትእዛዛት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሕጎች ናቸው። ይሁን እንጂ አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሌሎቹ ብዙ ሕጎችም በጣም አስፈላጊ ናቸው። ከእነዚህ ሕጎች መካከል አንዱ ‘ይሖዋ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አሳብህ፣ በፍጹም ነፍስህና በፍጹም ኃይልህ ውደድ’ ይላል። ሌላው ደግሞ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ይሖዋ ለሕዝቡ ከሰጣቸው ሕጎች ውስጥ ሁለቱ ታላላቅ ሕጎች እነዚህ እንደሆኑ ተናግሯል። ቆየት ብለን ስለ አምላክ ልጅና ስላስተማራቸው ትምህርቶች ብዙ ነገሮችን እንማራለን።