በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 43

ኢያሱ መሪ ሆነ

ኢያሱ መሪ ሆነ

ሙሴ ከእስራኤላውያን ጋር ወደ ከነዓን ምድር ለመግባት ፈልጎ ነበር። ስለዚህ ‘ይሖዋ ሆይ፣ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሬ መልካሚቱን ምድር እንዳይ ፍቀድልኝ’ ሲል ጠየቀ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ‘ዳግመኛ እንደዚህ ብለህ እንዳትጠይቀኝ!’ አለው። ይሖዋ እንደዚህ ያለው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?

ሙሴ አለቱን በመታበት ወቅት በተፈጸመው ሁኔታ የተነሳ ነው። በዚያ ጊዜ ሙሴና አሮን ለይሖዋ ክብር እንዳልሰጡ አስታውስ። ውኃውን ከአለቱ የሚያወጣው ይሖዋ መሆኑን ለሕዝቡ አልተናገሩም ነበር። በዚህ ምክንያት ይሖዋ ወደ ከነዓን ምድር እንዲገቡ እንደማይፈቅድላቸው ተናግሯል።

ስለዚህ አሮን ከሞተ ከጥቂት ወራት በኋላ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው:- ‘ኢያሱን ወስደህ በካህኑ በአልዓዛርና በሕዝቡ ፊት አቁመው። በእነርሱም ፊት አዲሱ መሪ ኢያሱ እንደሆነ ለሁሉም ተናገር።’ ሥዕሉ ላይ እንደምታየው ሙሴ ልክ ይሖዋ እንዳለው አድርጓል።

ከዚያም ይሖዋ ኢያሱን ‘አይዞህ፣ አትፍራ። እስራኤላውያንን ቃል ወደገባሁላቸው ወደ ከነዓን ምድር ታገባቸዋለህ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ’ አለው።

በኋላም ይሖዋ ሙሴን በሞዓብ ምድር ወደሚገኘው ወደ ናባው ተራራ ጫፍ እንዲወጣ ነገረው። ሙሴ እዚያ ላይ ሆኖ ከዮርዳኖስ ወንዝ ባሻገር ያለውን ውብ የከነዓን ምድር ማየት ይችላል። ይሖዋ እንዲህ አለው:- ‘ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ልጆች እሰጣቸዋለሁ ብዬ ቃል የገባሁላቸው ምድር ይህች ናት። በዓይንህ እንድታያት አደረግሁህ፣ ነገር ግን ወደዚያች አትሻገርም።’

ሙሴ በዚያው በናባው ተራራ ጫፍ ላይ ሞተ። ሙሴ ሲሞት 120 ዓመት ሆኖት ነበር። በዚህም ወቅት እንኳ ጠንካራ ሰው ነበር፤ የማየት ችሎታውም ጥሩ ነበር። ሕዝቡ ሙሴ በመሞቱ በጣም አዝነው አለቀሱ። ቢሆንም ኢያሱ አዲሱ መሪያቸው ሆኖ ስለተሾመላቸው ተደስተዋል።