በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 44

ረዓብ ሰላዮቹን ደበቀች

ረዓብ ሰላዮቹን ደበቀች

እነዚህ ሰዎች ችግር አጋጥሟቸዋል። ማምለጥ አለባቸው፤ አለዚያ መገደላቸው ነው። ሰዎቹ እስራኤላውያን ሰላዮች ናቸው፤ እነርሱን እየረዳቻቸው ያለችው ሴት ደግሞ ረዓብ ናት። ረዓብ ከኢያሪኮ ከተማ ግንብ ጋር በተያያዘው በዚህ ቤት ውስጥ ትኖር ነበር። እነዚህ ሰዎች ችግር ላይ ሊወድቁ የቻሉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመርምር።

እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ከነዓን ምድር ለመግባት ተዘጋጅተዋል። ወደዚያ ከመሻገራቸው በፊት ግን ኢያሱ ሁለት ሰላዮችን ላከ። ‘ሄዳችሁ ምድሪቱንና ኢያሪኮን ሰልሉ’ አላቸው።

ሰላዮቹ ኢያሪኮ ሲደርሱ ወደ ረዓብ ቤት ገቡ። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ‘ሁለት እስራኤላውያን ሰላዮች ምድሪቱን ሊሰልሉ ዛሬ ሌሊት ወደዚህ መጥተዋል’ በማለት ለኢያሪኮ ንጉሥ ነገረው። ንጉሡ ይህን ሲሰማ ወደ ረዓብ ሰዎችን ላከ፤ እነርሱም ‘ወደ ቤትሽ የገቡትን ሰዎች አውጪ!’ አሏት። ረዓብ ግን ሰላዮቹን በቤቷ ጣራ ውስጥ ደብቃቸው ነበር። ስለዚህ እንዲህ አለቻቸው:- ‘የሆኑ ሰዎች ወደ እኔ ቤት መጥተው ነበር፤ ከወዴት እንደመጡ ግን አላውቅም። መሸትሸት ሲልም የከተማዋ በር ከመዘጋቱ በፊት ወጥተው ሄዱ። በፍጥነት ከሄዳችሁ ልትደርሱባቸው ትችላላችሁ!’ ሰዎቹ ሰላዮቹን አሳደው ለመያዝ ሄዱ።

ሰዎቹ ከሄዱ በኋላ ረዓብ በፍጥነት ወደ ጣራው ወጣች። ሰላዮቹን እንዲህ አለቻቸው:- ‘ይሖዋ ይህን ምድር እንደሚሰጣችሁ አውቃለሁ። ከግብፅ ስትወጡ ቀይ ባሕርን እንዴት እንዳደረቀውና ሴዎንና ዐግ የተባሉትን ነገሥታት እንዴት እንዳጠፋችኋቸው ሰምተናል። እባካችሁ፣ እኔ ለእናንተ መልካም ነገር እንዳደረግሁላችሁ ሁሉ እናንተም ለእኔ መልካም እንደምታደርጉልኝ ቃል ግቡልኝ። አባቴንና እናቴን እንዲሁም ወንድሞቼንና እህቶቼን አድኑልኝ።’

ሰላዮቹ ያለችውን እንደሚያደርጉላት ቃል ገቡላት፤ ቢሆንም ረዓብ አንድ ነገር ማድረግ ነበረባት። ሰላዮቹ እንዲህ አሏት:- ‘ይህን ቀይ ገመድ መስኮትሽ ላይ እሰሪው፤ ዘመዶችሽን ሁሉ ወደ ቤትሽ ሰብስቢ። ኢያሪኮን ለመውሰድ ተመልሰን ስንመጣ ይህን ገመድ መስኮትሽ ላይ እናየዋለን፤ በቤትሽም ውስጥ ያለውን ሰው ሁሉ አንገድልም።’ ሰላዮቹ ወደ ኢያሱ ሲመለሱ የሆነውን ሁሉ ነገሩት።