በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 45

የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገር

የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገር

ተመልከት! እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ እየተሻገሩ ነው! ነገር ግን ውኃው የት አለ? ከፍተኛ ዝናብ የሚዘንብበት ወቅት ስለነበረ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ወንዙ ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር። አሁን ግን ያ ሁሉ ውኃ የለም! እስራኤላውያን ልክ በቀይ ባሕር እንዳደረጉት በደረቅ ምድር ላይ እየተሻገሩ ነው! ውኃው ሁሉ የት ሄደ? እስቲ እንመልከት።

እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ የሚሻገሩበት ጊዜ ሲደርስ ይሖዋ ኢያሱን የሚከተለውን ቃል ለሕዝቡ እንዲናገር አዘዘው:- ‘ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዘው ከእኛ ፊት ይሄዳሉ። እግሮቻቸውን በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ሲያስገቡ ውኃው መፍሰሱን ያቆማል።’

ስለዚህ ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አነሱና ተሸክመው ከሕዝቡ ፊት መሄድ ጀመሩ። ካህናቱ ዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ሲደርሱ እግሮቻቸውን ውኃው ውስጥ አስገቡ። ውኃው በኃይል ይፈስ ነበር፤ እንዲሁም ወደ ታች ጥልቅ ነበር። ቢሆንም እግሮቻቸው ውኃውን እንደረገጡ ወዲያውኑ ውኃው መፍሰሱን አቆመ! ተአምር ነበር! ይሖዋ ውኃውን ገድቦ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገው። ስለዚህ ብዙም ሳይቆይ ወንዙ ውስጥ የነበረው ውኃ ጠፋ!

የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ወደ ደረቀው ወንዝ መካከል ገቡ። ሥዕሉ ላይ ይታዩሃል? ካህናቱ መሀል ሲቆሙ እስራኤላውያን በሙሉ የዮርዳኖስን ወንዝ በደረቅ ምድር ተሻገሩ!

ሁሉም ከተሻገሩ በኋላ ይሖዋ ኢያሱን 12 ጠንካራ ሰዎች መርጦ የሚከተለውን እንዲነግራቸው አዘዘው:- ‘የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ወደቆሙበት ወደ ወንዙ መካከል ሂዱ። 12 ድንጋዮችን አንሡና በዚህ ሌሊት በምታድሩበት ቦታ አስቀምጧቸው። ወደፊት ልጆቻችሁ እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው? ብለው ሲጠይቋችሁ የይሖዋ የቃል ኪዳኑ ታቦት ዮርዳኖስን ሲሻገር ውኃው መፍሰሱን አቁሞ ነበር ትሏቸዋላችሁ። ድንጋዮቹ ይህን ተአምር ያስታውሷችኋል!’ በተጨማሪም ኢያሱ በወንዙ መካከል በሚገኘው ካህናቶቹ በቆሙበት ቦታ 12 ድንጋዮችን አቆመ።

በመጨረሻም ኢያሱ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙትን ካህናት ‘ከዮርዳኖስ ወንዝ ውጡ’ አላቸው። ካህናቱ እንደወጡ ወዲያውኑ ወንዙ እንደ ቀድሞው መፍሰስ ጀመረ።