በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 48

ጥበበኞቹ ገባዖናውያን

ጥበበኞቹ ገባዖናውያን

በከነዓን ምድር የሚገኙት ብዙዎቹ ከተሞች ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት ተዘጋጁ። ማሸነፍ የሚችሉ መስሏቸው ነበር። እስራኤላውያን በነበሩበት ቦታ አቅራቢያ በምትገኘው በገባዖን ከተማ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ግን እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ አልነበራቸውም። አምላክ እስራኤላውያንን እየረዳቸው እንዳለ ያምናሉ፤ ከአምላክ ጋር መዋጋት ደግሞ አልፈለጉም። ስለዚህ ገባዖናውያን ምን እንዳደረጉ ታውቃለህ?

በጣም ሩቅ ከሆነ ቦታ የመጡ ሰዎች መስለው ለመቅረብ ወሰኑ። ስለዚህ ከእነርሱ መካከል የተወሰኑ ሰዎች አሮጌ ልብስ ለበሱ፤ ያረጁ ጫማዎችንም አደረጉ። በአህያዎቻቸው ላይ ያረጁ ስልቻዎችን ጫኑ፤ የሻገተና የደረቀ እንጀራም ያዙ። ከዚያም ወደ ኢያሱ ሄዱና እንዲህ አሉት:- ‘እኛ የመጣነው ከሩቅ አገር ነው፤ ወደዚህ የመጣነው ስለ ታላቁ አምላካችሁ ስለ ይሖዋ ሰምተን ነው። በግብፅ ያደረገላችሁን ነገር ሁሉ ሰምተናል። ስለዚህ አለቆቻችን ለጉዞ የሚሆን ጥቂት ምግብ አዘጋጁና ወደ እነርሱ ሄዳችሁ “እኛ አገልጋዮቻችሁ ነን። እኛን እንደማትወጉን ቃል ግቡልን” በሏቸው አሉን። ረጅም ጉዞ በመጓዛችን የተነሳ ይኸው ልብሶቻችን አርጅተዋል፤ እንጀራችንም ሻግቶ ደርቋል።’

ኢያሱና ሌሎቹ አለቆች ገባዖናውያንን አመኗቸው። ስለዚህ እነርሱን እንደማይወጓቸው ቃል ገቡላቸው። ከሦስት ቀናት በኋላ ግን ገባዖናውያን በአቅራቢያቸው የሚኖሩ ሰዎች መሆናቸውን አወቁ።

ኢያሱ ‘ከሩቅ አገር ነው የመጣነው ያላችሁን ለምንድን ነው?’ ብሎ ጠየቃቸው።

ገባዖናውያኑም ‘ይህን ያደረግነው አምላካችሁ ይሖዋ ይህን የከነዓን ምድር በሙሉ እሰጣችኋለሁ ብሎ ቃል እንደገባላችሁ ስለ ሰማን ነው። ስለዚህ እንዳታጠፉን ፈራን’ ብለው መለሱለት። ሆኖም እስራኤላውያን የገቡትን ቃል ጠብቀዋል፤ ገባዖናውያንን አላጠፏቸውም። በዚያ ፋንታ አገልጋዮቻቸው አደረጓቸው።

የኢየሩሳሌም ንጉሥ ገባዖናውያን ከእስራኤላውያን ጋር ዕርቅ በመፍጠራቸው ተናደደ። ስለዚህ ሌሎች አራት ነገሥታትን ‘ገባዖናውያንን መውጋት እንድችል ኑና እርዱኝ’ አላቸው። እነዚህ አምስት ነገሥታት ገባዖናውያንን ለመውጋት ተነሱ። ገባዖናውያን እነዚህ ነገሥታት እነርሱን ለመውጋት እንዲነሱ ያደረጋቸውን ዕርቅ ከእስራኤላውያን ጋር መፍጠራቸው ጥበብ ነበርን? እስቲ እንመልከት።