በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 52

ጌዴዎንና 300 ተዋጊዎቹ

ጌዴዎንና 300 ተዋጊዎቹ

ሥዕሉ ላይ ምን እየተደረገ እንዳለ ታያለህ? እነዚህ ሰዎች በሙሉ የእስራኤል ተዋጊዎች ናቸው። ወደ ታች ያጎነበሱት ሰዎች ውኃ እየጠጡ ነው። አጠገባቸው የቆመው ሰው መስፍኑ ጌዴዎን ነው። ሰዎቹ ውኃውን እንዴት እየጠጡ እንዳሉ እየተመለከተ ነው።

ሰዎቹ የሚጠጡበትን የተለያየ መንገድ በደንብ ተመልከት። አንዳንዶቹ ውኃው ላይ ተደፍተው እየጠጡ ነው። አንዱ ግን በአካባቢው ምን እየተፈጸመ እንዳለ ማየት እንዲችል ውኃውን በእጁ ይዞ እየጠጣ ነው። ይህ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ ጌዴዎንን በአካባቢያቸው ያለውን ሁኔታ እየተመለከቱ የሚጠጡትን ብቻ እንዲመርጥ ነግሮት ነበር። አምላክ የተቀሩት ሰዎች ወደ ቤታቸው ይመለሱ በማለት ተናግሮ ነበር። ይህ የሆነበትን ምክንያት እስቲ እንመልከት።

እስራኤላውያን እንደገና ብዙ ችግር አጋጥሟቸው ነበር። ይህ የሆነው ይሖዋን ባለመታዘዛቸው ነበር። የምድያም ሰዎች በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው እያሠቃዩአቸው ነበር። ስለዚህ እስራኤላውያን ይሖዋ እንዲረዳቸው ወደ እርሱ ጮኹ፤ ይሖዋም ልመናቸውን ሰማ።

ይሖዋ ጌዴዎንን የጦር ሠራዊት እንዲሰበስብ አዘዘው፤ ጌዴዎንም 32, 000 ተዋጊዎችን አንድ ላይ ሰበሰበ። እስራኤልን የሚገጥመው ሠራዊት ግን 135, 000 ሰዎችን ያቀፈ ነበር። ያም ሆኖ ግን ይሖዋ ጌዴዎንን ‘የሰበሰብካቸው ሰዎች ብዙ ናቸው’ አለው። ይሖዋ እንዲህ ያለው ለምን ነበር?

እስራኤላውያን በጦርነቱ ካሸነፉ በራሳቸው ችሎታ ያሸነፉ መስሎ ሊታያቸው ስለሚችል ነው። ድል ለማድረግ የይሖዋ እርዳታ አያስፈልገንም ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ስለዚህ ይሖዋ ጌዴዎንን ‘የፈሩ ሰዎች በሙሉ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ንገራቸው’ አለው። ጌዴዎን ይህን ሲናገር 22, 000 ተዋጊዎቹ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እነዚህ ተዋጊዎች ሲመለሱ ከእነዚያ 135, 000 ወታደሮች ጋር ለመዋጋት ከእርሱ ጋር የቀሩት ሰዎች 10, 000 ብቻ ሆኑ።

ሆኖም ይሖዋ ‘አሁንም ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው’ አለው። ስለዚህ ጌዴዎን ሰዎቹን ከዚህ ወንዝ እንዲጠጡ ካደረገ በኋላ ውኃው ላይ ተደፍተው የሚጠጡትን ሰዎች ሁሉ ወደ ቤታቸው እንዲመልሳቸው ይሖዋ አዘዘው። ‘ቀና ብለው እየተመለከቱ ይጠጡ በነበሩት 300 ሰዎች አማካኝነት እንድታሸንፍ እረዳሃለሁ’ በማለት ይሖዋ ቃል ገባለት።

ውጊያው የሚካሄድበት ጊዜ ደረሰ። ጌዴዎን ከእርሱ ጋር የነበሩትን 300 ሰዎች በሦስት ቡድን ከፈላቸው። ለሁሉም ቀንደ መለከትና በውስጡ ችቦ የያዘ ማሰሮ ሰጣቸው። እኩለ ሌሊት ሊሆን ሲል ሁሉም በጠላት ወታደሮች ሠፈር ዙሪያ ተሰባሰቡ። ከዚያም ሁሉም ቀንደ መለከታቸውን ነፉና ማሰሮዎቻቸውን ሰባበሩ፤ እንዲሁም ‘የይሖዋና የጌዴዎን ሰይፍ!’ ብለው ጮኹ። የጠላት ወታደሮች ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ግራ ተጋቡና ደነገጡ። ሁሉም መሸሽ ጀመሩ፤ እስራኤላውያንም በውጊያው አሸነፉ።

መሳፍንት ምዕራፍ 6 እስከ 8