በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 53

ዮፍታሔ የገባው ቃል

ዮፍታሔ የገባው ቃል

ቃል ከገባህ በኋላ የገባኸውን ቃል መጠበቅ አስቸጋሪ ሆኖብህ ያውቃል? እዚህ ሥዕል ላይ የምታየው ሰው ይህ ሁኔታ አጋጥሞታል፤ በጣም ያዘነውም በዚህ ምክንያት ነው። ይህ ሰው ደፋሩ የእስራኤል መስፍን ዮፍታሔ ነው።

ዮፍታሔ ይኖር የነበረው እስራኤላውያን ይሖዋን ማምለክ ትተው በነበረበት ዘመን ነበር። እስራኤላውያን እንደገና መጥፎ ነገር እየሠሩ ነበር። ስለዚህ ይሖዋ የአሞን ሰዎች እንዲያሠቃዩአቸው ፈቀደ። ይህም እስራኤላውያን ‘በአንተ ላይ ኃጢአት ሠርተናል። እባክህ አድነን!’ ብለው ወደ ይሖዋ እንዲጮኹ አደረጋቸው።

ሕዝቡ መጥፎ ነገር በመሥራታቸው ተጸጸቱ። ይሖዋን እንደገና በማምለክ በሠሩት ሥራ መጸጸታቸውን በተግባር አሳዩ። ስለዚህ ይሖዋ እንደገና ረዳቸው።

ሕዝቡ መጥፎዎቹን አሞናውያንን እንዲወጋላቸው ዮፍታሔን መረጡት። ዮፍታሔ ይሖዋ በውጊያው እንዲረዳው በጣም ፈልጎ ነበር። ስለዚህ እንዲህ ሲል ለይሖዋ ቃል ገባ:- ‘አሞናውያንን እንዳሸንፍ ካደረግኸኝ ስመለስ እኔን ለመቀበል ከቤቴ መጀመሪያ የሚወጣውን ሰው ለአንተ እሰጠዋለሁ።’

ይሖዋ ዮፍታሔ የገባውን ቃል ሰምቶ ድል እንዲያገኝ ረዳው። ዮፍታሔ ወደ ቤቱ ሲመለስ እሱን ለመቀበል መጀመሪያ የወጣው ሰው ማን እንደሆነ ታውቃለህ? ሴት ልጁ ነች፤ ከእሷ ሌላ ልጅ የለውም። ‘ወይኔ ልጄ!’ በማለት ዮፍታሔ ጮኸ። ‘ምን ዓይነት ሐዘን ነው ያመጣሽብኝ! አንዴ ለይሖዋ ቃል ገብቻለሁ፤ የገባሁትን ቃል ማፍረስ አልችልም።’

የዮፍታሔ ልጅ የገባውን ቃል ስትሰማ በመጀመሪያ እሷም አዝና ነበር። ምክንያቱም አባቷንና ጓደኞቿን ትታ መሄዷ ነው። ይሁን እንጂ ቀሪውን ሕይወቷን በሴሎ በሚገኘው በማደሪያው ድንኳን ይሖዋን በማገልገል ታሳልፋለች። ስለዚህ አባቷን ‘ለይሖዋ ቃል ከገባህ ቃልህን መጠበቅ አለብህ’ አለችው።

የዮፍታሔ ልጅ ወደ ሴሎ ሄደችና ቀሪውን ሕይወቷን በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ይሖዋን በማገልገል አሳለፈች። የእስራኤል ሴቶች እሷን ለመጠየቅ በየዓመቱ ለአራት ቀናት ወደዚያ ይሄዱና አንድ ላይ ሆነው አስደሳች የሆነ ጊዜ ያሳልፉ ነበር። የዮፍታሔ ልጅ ጥሩ የይሖዋ አገልጋይ ስለነበረች ሕዝቡ ይወዷት ነበር።