በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 54

ኃይለኛው ሰው

ኃይለኛው ሰው

በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ኃይለኛ የነበረው ሰው ማን እንደሆነ ታውቃለህ? ሳምሶን የተባለ አንድ መስፍን ነው። ሳምሶንን ኃይል የሰጠው ይሖዋ ነው። ሳምሶን ከመወለዱ በፊት እንኳ ይሖዋ እናቱን ‘በቅርቡ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ። እስራኤላውያንንም ከፍልስጤማውያን ያድናል’ ብሏታል።

ፍልስጤማውያን በከነዓን ይኖሩ የነበሩ መጥፎ ሰዎች ናቸው። ብዙ ተዋጊዎች ነበሯቸው፤ እስራኤላውያንንም ያሠቃዩአቸው ነበር። አንድ ቀን ሳምሶን ፍልስጤማውያን ወደሚኖሩበት ቦታ ሲሄድ አንድ ትልቅ አንበሳ ወደ እርሱ እያገሣ መጣ። ሆኖም ሳምሶን ምንም ነገር ሳይዝ አንበሳውን በእጁ ብቻ ገደለው። በመቶዎች የሚቆጠሩ መጥፎ ፍልስጤማውያንንም ገድሏል።

ከጊዜ በኋላ ሳምሶን ደሊላ የምትባል አንዲት ሴት ወደደ። የፍልስጤማውያን አለቆች ሳምሶንን በጣም ኃይለኛ እንዲሆን ያደረገው ነገር ምን እንደሆነ ከነገርሽን እያንዳንዳችን 1, 100 የብር ሳንቲሞች እንሰጥሻለን ብለው ቃል ገቡላት። ደሊላ ይህን ገንዘብ ማግኘት ፈለገች። የሳምሶንም ሆነ የአምላክ ሕዝቦች እውነተኛ ጓደኛ አልነበረችም። ስለዚህ ሳምሶን በጣም ኃይለኛ እንዲሆን ያደረገው ነገር ምን እንደሆነ እንዲነግራት ጨቀጨቀችው።

በመጨረሻ ደሊላ ሳምሶን ይህን ኃይል ያገኘበትን ምስጢር እንዲነግራት አደረገችው። ‘ከተወለድኩ ጀምሮ ፀጉሬ ተቆርጦ አያውቅም፤ አምላክ ልዩ አገልጋዩ ማለትም ናዝራዊ ሆኜ እንዳገለግለው መርጦኛል። ፀጉሬ ከተቆረጠ አሁን ያለኝ ኃይል ይጠፋል’ አላት።

ይህን ሲነግራት ደሊላ ሳምሶን ጭኗ ላይ እንዲተኛና እንቅልፍ እንዲወስደው አደረገች። ከዚያም አንድ ሰው ጠራችና ፀጉሩን እንዲቆርጠው አደረገች። ሳምሶን ከእንቅልፉ ሲነቃ ኃይሉ ጠፍቶ ነበር። ከዚያ በኋላ ፍልስጤማውያን መጡና ያዙት። ሁለቱንም ዓይኖቹን አወጧቸውና ባሪያቸው አደረጉት።

ከዕለታት አንድ ቀን ፍልስጤማውያን አምላካቸውን ዳጎንን ለማምለክ አንድ ትልቅ ድግስ አዘጋጁና ሳምሶንን ከእስር ቤት አምጥተው ያሾፉበት ጀመር። በዚህ ወቅት የሳምሶን ፀጉር እንደገና አድጎ ነበር። ሳምሶን እጁን ይዞ የሚመራውን ልጅ ‘ሕንጻውን ደግፈው የያዙትን ምሰሶች አስይዘኝ’ አለው። ከዚያም ሳምሶን ይሖዋ ኃይል እንዲሰጠው ጸለየና ምሰሶዎቹን ያዘ። ‘ከእነዚህ ፍልስጤማውያን ጋር ልሙት’ ብሎ ተናገረ። በድግሱ ላይ 3, 000 ፍልስጤማውያን ተገኝተው ነበር፤ ሳምሶን አጎንብሶ ምሰሶዎቹን ሲገፋቸው ሕንጻው ተደረመሰና እነዚህን መጥፎ ሰዎች በሙሉ ገደላቸው።