በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 55

አምላክን ያገለገለ አንድ ትንሽ ልጅ

አምላክን ያገለገለ አንድ ትንሽ ልጅ

ይህ ትንሽ ልጅ ደስ አይልም? ሳሙኤል ይባላል። የሳሙኤልን ራስ በእጁ የያዘው ሰው የእስራኤል ሊቀ ካህን የሆነው ዔሊ ነው። ሳሙኤልን ወደ ዔሊ ያመጡት ደግሞ አባቱ ሕልቃናና እናቱ ሐና ናቸው።

ሳሙኤል ገና አራት ወይም አምስት ዓመት ቢሆነው ነው። ቢሆንም በዚህ በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ከዔሊና ከሌሎች ካህናት ጋር ሊኖር ነው። ሕልቃናና ሐና ገና ትንሽ ልጅ የሆነውን ሳሙኤልን ይሖዋን በማደሪያው ድንኳን እንዲያገለግል ያመጡት ለምንድን ነው? እስቲ እንመልከት።

ይህ ከመሆኑ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሐና በጣም አዝና ነበር። አዝና የነበረው ልጅ መውለድ ባለመቻሏ ነበር፤ ልጅ ለመውለድ በጣም ትፈልግ ነበር። ስለዚህ አንድ ቀን ሐና ወደ ይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ሄዳ በነበረበት ወቅት ‘አቤቱ ይሖዋ፣ አትርሳኝ! ወንድ ልጅ ከሰጠኸኝ ዕድሜውን ሙሉ እንዲያገለግልህ ለአንተ እሰጠዋለሁ’ ብላ ጸለየች።

ይሖዋ የሐናን ጸሎት ሰማና ከጥቂት ወራት በኋላ ሳሙኤልን ወለደች። ሐና ትንሹን ልጅዋን ትወድደው ነበር፤ ገና በጣም ትንሽ እያለም ስለ ይሖዋ ታስተምረው ጀመር። ‘ሳሙኤል ጡት መጥባት እንዳቆመ ይሖዋን እንዲያገለግል ወደ ማደሪያው ድንኳን እወስደዋለሁ’ ብላ ለባልዋ ነገረችው።

በሥዕሉ ላይ እንደምናየው ሐናና ሕልቃና ሳሙኤልን ወደ ማደሪያው ድንኳን ይዘውት መጡ። ሳሙኤል ወላጆቹ በደንብ ስላስተማሩት በዚህ በይሖዋ ድንኳን ይሖዋን ለማገልገል በመቻሉ ተደስቷል። በየዓመቱ ሕልቃናና ሐና የአምልኮ ሥርዓት ለመፈጸምና ትንሹን ልጃቸውን ለመጠየቅ ወደዚህ ልዩ ድንኳን ይመጡ ነበር። በየዓመቱም ሐና ለሳሙኤል አዲስ ካባ እየሠራች ታመጣለት ነበር።

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ሳሙኤል ይሖዋን በማደሪያው ድንኳን ማገልገሉን ቀጠለ፤ ይሖዋም ሆነ ሕዝቡ ወደዱት። የሊቀ ካህኑ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ ግን ጥሩ ሰዎች አልነበሩም። ብዙ መጥፎ ነገሮች ይሠሩ ነበር፤ ሌሎችም የይሖዋን ሕግ እንዲጥሱ አድርገዋል። ዔሊ ከክህነት ሥራቸው ሊያስወግዳቸው ይገባ ነበር፤ ነገር ግን እንዲህ አላደረገም።

ወጣቱ ሳሙኤል በማደሪያው ድንኳን የሚፈጸመው ማንኛውም መጥፎ ድርጊት ይሖዋን ማገልገሉን እንዲያቆም አላደረገውም። ይሖዋን ከልባቸው የሚወዱት ሰዎች በጣም ጥቂት ስለነበሩ ይሖዋ ሰውን ካነጋገረ ረጅም ጊዜ አልፎ ነበር። ሳሙኤል ትንሽ አደግ ካለ በኋላ የሚከተለው ሁኔታ ተፈ⁠ጸመ:-

ሳሙኤል በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ተኝቶ እያለ አንድ ድምፅ ቀሰቀሰው። ሳሙኤል ‘አቤት’ ብሎ መለሰ። ተነሣና ወደ ዔሊ ሄዶ ‘ይኸው መጥቻለሁ’ አለ።

ዔሊ ግን ‘አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ’ አለው። ስለዚህ ሳሙኤል ተመልሶ ተኛ።

ከዚያም ለሁለተኛ ጊዜ ‘ሳሙኤል!’ የሚል ድምፅ ሰማ። ሳሙኤል እንደገና ተነሣና ወደ ዔሊ ሄደ። ‘ይኸው መጥቻለሁ’ አለው። ይሁን እንጂ ዔሊ ‘ልጄ ሆይ፣ አልጠራሁህም። ተመልሰህ ተኛ’ አለው። ስለዚህ ሳሙኤል ወደ አልጋው ተመለሰ።

ለሦስተኛ ጊዜ ‘ሳሙኤል!’ የሚል ድምፅ ሰማ። ስለዚህ ሳሙኤል ወደ ዔሊ ሄደ። ‘ይኸው መጥቻለሁ፤ አሁንስ ጠርተኸኝ መሆን አለበት’ አለው። በዚህ ጊዜ ዔሊ እየጠራው ያለው ይሖዋ መሆን እንዳለበት አወቀ። ስለዚህ ሳሙኤልን ‘ሂድና ተኛ፤ እንደገና ከጠራህ “ይሖዋ ሆይ፣ አገልጋይህ ይሰማልና ተናገር” በለው’ ሲል ነገረው።

ሳሙኤል ይሖዋ እንደገና ሲጠራው የተባለውን አደረገ። ከዚያም ይሖዋ ዔሊንና ልጆቹን እንደሚቀጣቸው ለሳሙኤል ነገረው። ከጊዜ በኋላ አፍኒንና ፊንሐስ ከፍልስጤማውያን ጋር በተደረገው ውጊያ ላይ ሞቱ፤ ዔሊም የተፈጸመውን ሁኔታ ሲሰማ ወደቀና አንገቱ ተሰብሮ ሞተ። ስለዚህ የይሖዋ ቃል ተፈጸመ።

ሳሙኤል አደገና የመጨረሻው የእስራኤል መስፍን ሆነ። ሳሙኤል ሲሸመግል ሕዝቡ ‘የሚገዛን ንጉሥ አንግሥልን’ ብለው ጠየቁት። ሳሙኤል ይህን ማድረግ አልፈለገም፤ ምክንያቱም ንጉሣቸው ይሖዋ ነበር። ሆኖም ይሖዋ ሕዝቡ ያሉትን እንዲያደርግላቸው አዘዘው።