በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 4

ከመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ እስከ ባቢሎን ምርኮ

ከመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ እስከ ባቢሎን ምርኮ

ሳኦል የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሆነ። በኋላ ግን ይሖዋ ሳኦልን ተወው፤ ዳዊት በእሱ ምትክ ንጉሥ እንዲሆን ተመረጠ። ስለ ዳዊት ብዙ የምንማራቸው ነገሮች ይኖራሉ። ገና ወጣት ሳለ ከግዙፉ ጎልያድ ጋር ተዋግቷል። ከጊዜ በኋላም ከቀናተኛው ንጉሥ ከሳኦል ሸሽቷል። ከዚያም ቆንጆዋ ሴት አቢግያ ዳዊት ጥበብ የጎደለው ነገር እንዳይፈጽም አድርጋዋለች።

ቀጥሎ ደግሞ ዳዊትን በመተካት በእስራኤል ላይ ስለነገሠው የዳዊት ልጅ ስለ ሰሎሞን ብዙ ነገሮችን እንማራለን። የመጀመሪያዎቹ ሦስት የእስራኤል ነገሥታት እያንዳንዳቸው ለ40 ዓመታት ገዝተዋል። ሰሎሞን ከሞተ በኋላ እስራኤል የሰሜን መንግሥትና የደቡብ መንግሥት ተብሎ በሁለት መንግሥታት ተከፈለ።

አሥር ነገዶችን ያቀፈው የሰሜኑ መንግሥት በአሦራውያን እስከ ተደመሰሰበት ጊዜ ድረስ ለ257 ዓመታት ቆይቷል። ከዚያም 133 ዓመታት ካለፉ በኋላ ሁለት ነገዶችን ያቀፈው የደቡቡ መንግሥት ጠፋ። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ወደ ባቢሎን ተማረኩ። ስለዚህ ክፍል አራት ብዙ አስደሳች ክንውኖች የምንቃኝበትን የ510 ዓመታት ታሪክ ይዟል።