በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 56

የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ሳኦል

የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ሳኦል

ሳሙኤል በሰውየው ራስ ላይ ዘይት ሲያፈስ ተመልከት። በዚያ ዘመን አንድ ሰው ንጉሥ ሆኖ መሾሙን ለማሳየት እንዲህ ያደርጉ ነበር። ሳሙኤል በሳኦል ራስ ላይ ዘይት እንዲያፈስ ይሖዋ አዘዘው። ዘይቱ ደስ የሚል ሽታ ያለው ልዩ ዘይት ነበር።

ሳኦል ንጉሥ ለመሆን የሚያስችል ብቃት አለኝ ብሎ አላሰበም ነበር። ለሳሙኤል ‘እኔ በእስራኤል ካሉት ነገዶች ሁሉ በጣም አነስተኛ ከሆነው ከብንያም ነገድ የተወለድኩ ሰው ነኝ። ንጉሥ ትሆናለህ ለምን ትለኛለህ?’ አለው። ሳኦል ራሱን ከፍ ከፍ ባለማድረጉ ይሖዋ ወዶታል። ንጉሥ እንዲሆን የመረጠውም ለዚህ ነው።

ይሁን እንጂ ሳኦል ድሃ ወይም ኮስማና ሰው አልነበረም። ከሃብታም ቤተሰብ የተወለደ፣ በጣም ቆንጆና ረጅም ሰው ነበር። በእስራኤል ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ረጅም ነበር! በተጨማሪም ሳኦል በጣም ፈጣን ሯጭ እንዲሁም በጣም ጠንካራ ሰው ነበር። ይሖዋ ሳኦል ንጉሥ እንዲሆን ስለመረጠው ሕዝቡ በጣም ተደሰቱ። ሕዝቡ ሁሉ ‘ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!’ እያሉ ጮኹ።

የእስራኤል ጠላቶች ከምንጊዜውም ይበልጥ በርትተውባቸው ነበር። በዚህም ወቅት በእስራኤላውያን ላይ ብዙ ችግር እያደረሱባቸው ነበር። ሳኦል ንጉሥ ከሆነ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አሞናውያን ሊወጓቸው መጡ። ይሁን እንጂ ሳኦል አንድ ትልቅ ሠራዊት ሰበሰበና በአሞናውያን ላይ ድል ተቀዳጀ። ይህም ሕዝቡ ሳኦል በመንገሡ እንዲደሰቱ አደረጋቸው።

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ሳኦል እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ላይ ብዙ ድል እንዲቀዳጁ አደረጋቸው። በተጨማሪም ሳኦል ዮናታን የተባለ ደፋር ልጅ ነበረው። ዮናታንም እስራኤላውያን በብዙ ውጊያዎች እንዲያሸንፉ ረድቷቸዋል። በዚህም ወቅት ፍልስጤማውያን የእስራኤላውያን ቀንደኛ ጠላት ነበሩ። ከዕለታት አንድ ቀን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን እስራኤላውያንን ለመውጋት መጡ።

ሳሙኤል እሱ እስኪመጣና ለይሖዋ መሥዋዕት ወይም ስጦታ እስኪያቀርብ ድረስ እንዲጠብቅ ሳኦልን አዘዘው። ይሁን እንጂ ሳሙኤል ዘገየ። ሳኦል ፍልስጤማውያን ውጊያውን እንዳይጀምሩ ፈራ፤ ስለዚህ መሥዋዕቱን ራሱ አቀረበ። በመጨረሻ ሳሙኤል ሲመጣ ሳኦልን የይሖዋን ትእዛዝ እንደጣሰ ነገረው። ሳሙኤል ‘ይሖዋ በእስራኤል ላይ የሚነግሥ ሌላ ሰው ይመርጣል’ አለው።

ከጊዜ በኋላ ሳኦል እንደገና የይሖዋን ትእዛዝ ጣሰ። ስለዚህ ሳሙኤል እንዲህ አለው:- ‘ይሖዋን መታዘዝ ምርጥ የሆነ በግ መሥዋዕት አድርጎ ከማቅረብ ይበልጣል። የይሖዋን ትእዛዝ ስለጣስክ ይሖዋ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆነህ እንድትቀጥል አይፈቅድልህም።’

እኛ ከዚህ ጥሩ ትምህርት መማር እንችላለን። ይሖዋን ዘወትር መታዘዝ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳየናል። በተጨማሪም ልክ እንደ ሳኦል ጥሩ የነበረ ሰው ሊለወጥና መጥፎ ሰው ሊሆን እንደሚችል ያሳያል። እኛ መጥፎ ሰዎች መሆን አንፈልግም፤ እንፈልጋለን እንዴ?