በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 61

ዳዊት ነገሠ

ዳዊት ነገሠ

ሳኦል እንደገና ዳዊትን ለመያዝ ሞከረ። 3, 000 ምርጥ ወታደሮቹን ሰበሰበና ዳዊትን መፈለግ ጀመረ። ዳዊት ይህን ሲሰማ ሳኦልና አብረውት ያሉት ሰዎች ሌሊት የት እንደሰፈሩ ለማወቅ ሰላዮችን ላከ። ከዚያም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሁለት ሰዎች ‘ከእናንተ መካከል ከእኔ ጋር ሳኦል ወዳለበት ቦታ የሚሄድ ማን ነው?’ ብሎ ጠየቃቸው።

አቢሳ ‘እኔ እሄዳለሁ’ ብሎ መለሰ። አቢሳ የዳዊት እህት የጽሩያ ልጅ ነው። ሳኦልና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ተኝተው እያለ ዳዊትና አቢሳ ኮቴያቸውን ሳያሰሙ ቀስ ብለው ወደ ሰፈሩበት ቦታ ገቡ። ከሳኦል ራስ አጠገብ ተቀምጠው የነበሩትን የሳኦልን ጦርና የውኃ ኮዳውን አነሱ። ሁሉም ኃይለኛ እንቅልፍ ወስዷቸው ስለነበረ ያያቸውም ሆነ የሰማቸው አልነበረም።

አሁን ዳዊትንና አቢሳን ተመልከት። ማንም ሳያያቸው ሄደው በአንድ ኮረብታ ጫፍ ላይ ቆመዋል። ዳዊት ጮክ ብሎ የእስራኤልን ሠራዊት አለቃ እንዲህ አለው:- ‘አበኔር ሆይ፣ ጌታህን ንጉሡን የማትጠብቀው ለምንድን ነው? እስቲ ተመልከት! የንጉሡ ጦርና የውኃ ኮዳው የት አለ?’

ሳኦል ከእንቅልፉ ነቃ። የዳዊት ድምፅ እንደሆነ አወቀና ‘ዳዊት ነህን?’ ብሎ ጠየቀው። ሳኦልና አበኔር ታች ቆመው ይታዩሃል?

‘አዎ፣ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ ዳዊት ነኝ’ በማለት ዳዊት ለሳኦል መለሰለት። ከዚያም ዳዊት እንዲህ ሲል ጠየቀው:- ‘የምታሳድደኝ ለምንድን ነው? ምን ክፉ ነገር ሠራሁ? ንጉሥ ሆይ፣ ጦርህ ያለው እኔ ጋር ነው። አንድ ሰው ይምጣና ይውሰደው።’

ሳኦል ‘በድያለሁ፤ የሠራሁት ሁሉ የሞኝ ሥራ ነው’ በማለት የሠራውን ስህተት አመነ። ከዚያ በኋላ ዳዊት ወደሚሸሸግበት ቦታ ሄደ፤ ሳኦል ደግሞ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ይሁን እንጂ ዳዊት ‘አንድ ቀን ሳኦል ሊገድለኝ ይችላል። ስለዚህ ወደ ፍልስጤማውያን ምድር መሸሽ አለብኝ’ ብሎ አሰበ። ያደረገውም ይህንኑ ነበር። ዳዊት ፍልስጤማውያንን አታለላቸውና ከእነርሱ ጎን እንደቆመ አድርገው እንዲያስቡ አደረጋቸው።

የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ ፍልስጤማውያን ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት ዘመቱ። በውጊያው ሳኦልና ዮናታን ተገደሉ። ዳዊት ይህን ሲሰማ በጣም አዘነ፤ በዚህም ምክንያት አንድ በጣም ጥሩ መዝሙር ጻፈ። በዚህ መዝሙር ላይ ዳዊት ‘ወንድሜ ዮናታን ሆይ፣ ስለ አንተ እጅግ አዝናለሁ። በጣም እወድህ ነበር!’ ሲል ዘምሯል።

ከዚህ በኋላ ዳዊት እስራኤል ውስጥ ወደምትገኘው ወደ ኬብሮን ከተማ ተመለሰ። የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ እንዲነግሥ በሚፈልጉ ሰዎችና ዳዊት እንዲነግሥ በሚፈልጉ ሰዎች መካከል ጦርነት ነበር። ይሁን እንጂ በመጨረሻ ዳዊትን ይደግፉ የነበሩት ሰዎች አሸነፉ። ዳዊት ሲነግሥ 30 ዓመቱ ነበር። በኬብሮን ሰባት ዓመት ተኩል ነገሠ። እዚያ ሳለ ከተወለዱለት ወንዶች ልጆች መካከል አምኖን አቤሴሎምና አዶንያስ ይገኙበታል።

ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ኢየሩሳሌም የምትባለውን ውብ ከተማ ለመያዝ ዘመቱ። የዳዊት እህት የጽሩያ ሌላው ልጅ ኢዮአብ የውጊያው መሪ ነበር። በዚህም ምክንያት ዳዊት ኢዮአብን የሠራዊቱ አለቃ አደረገው። ከዚህ በኋላ ዳዊት በኢየሩሳሌም ከተማ መግዛት ጀመረ።