በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 62

በዳዊት ቤት ውስጥ ችግር ተፈጠረ

በዳዊት ቤት ውስጥ ችግር ተፈጠረ

ዳዊት በኢየሩሳሌም መግዛት ከጀመረ በኋላ ይሖዋ ሠራዊቱን በጠላቶቻቸው ላይ ብዙ ድል አቀዳጃቸው። ይሖዋ የከነዓንን ምድር ለእስራኤላውያን እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶ ነበር። ስለዚህ አሁን በይሖዋ እርዳታ ቃል የገባላቸውን ምድር በሙሉ ወረሱ።

ዳዊት ጥሩ ገዥ ነበር። ይሖዋን ይወዳል። በመሆኑም ኢየሩሳሌምን ከያዘ በኋላ በመጀመሪያ ካደረጋቸው ነገሮች መካከል አንዱ የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ማምጣት ነበር። በተጨማሪም ታቦቱን የሚያስቀምጥበት ቤተ መቅደስ መሥራት ፈለገ።

ዳዊት ትልቅ ሰው ከሆነ በኋላ አንድ ከባድ ስህተት ሠራ። ዳዊት የሌላ ሰው የሆነን ነገር መውሰድ ስህተት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ቀን ምሽት በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ሆኖ ወደ ታች ሲመለከት አንድ በጣም ቆንጆ የሆነች ሴት ተመለከተ። ይህች ሴት ቤርሳቤህ ትባላለች፤ ባልዋ ደግሞ ከዳዊት ወታደሮች አንዱ የሆነው ኦርዮ የሚባል ሰው ነው።

ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር የጾታ ግንኙነት የመፈጸም ከፍተኛ ፍላጎት ስላደረበት ወደ ቤተ መንግሥቱ እንድትመጣ አደረገ። ባልዋ በውጊያ ላይ ነበር። ዳዊት ከእሷ ጋር የጾታ ግንኙነት ፈጸመ፤ ከጊዜ በኋላም ቤርሳቤህ እንዳረገዘች አወቀች። ዳዊት በጣም ስለተጨነቀ ኦርዮ እንዲገደል በውጊያው ግንባር ላይ እንዲያሰልፈው ለሠራዊቱ አለቃ ለኢዮአብ መልእክት ላከበት። ኦርዮ ሲገደል ዳዊት ቤርሳቤህን አገባት።

ይሖዋ በዳዊት በጣም ተቆጣ። ስለዚህ የሠራቸውን ኃጢአቶች እንዲነግረው አገልጋዩን ናታንን ላከው። ሥዕሉ ላይ እንደምታየው ናታን ዳዊትን እያነጋገረው ነው። ዳዊት በሠራው ሥራ በጣም አዘነ፤ በመሆኑም ይሖዋ ዳዊትን እንዲሞት አላደረገውም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ‘እነዚህን መጥፎ ነገሮች ስለ ሠራህ በቤትህ ውስጥ ብዙ ችግር ይፈጠራል’ አለው። በእርግጥም ዳዊት ብዙ ችግር ገጥሞት ነበር!

በመጀመሪያ የቤርሳቤህ ልጅ ሞተ። ከዚያም የዳዊት የበኩር ልጅ የሆነው አምኖን እህቱ ትዕማር ብቻዋን ከእርሱ ጋር እንድትሆን ካደረገ በኋላ አስገድዷት ከእርሷ ጋር የጾታ ግንኙነት ፈጸመ። የዳዊት ልጅ አቤሴሎም በዚህ ድርጊት በጣም በመናደዱ አምኖንን ገደለው። ከጊዜ በኋላ አቤሴሎም በብዙ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅነትን አገኘና ራሱን ንጉሥ አደረገ። በመጨረሻ ከአቤሴሎም ጋር በተደረገው ጦርነት ዳዊት አሸነፈና አቤሴሎም ተገደለ። አዎ፣ ዳዊት ብዙ ችግር አጋጥሞታል።

በዚህ ሁሉ መካከል ቤርሳቤህ ሰሎሞን የሚባል ልጅ ወለደች። ዳዊት ሲያረጅና ሲታመም ልጁ አዶንያስ ራሱን ንጉሥ ለማድረግ ሞከረ። በዚህ ጊዜ ዳዊት ሰሎሞን ንጉሥ እንደሚሆን ለማሳየት ሳዶቅ የተባለ ካህን በራሱ ላይ ዘይት እንዲያፈስበት አደረገ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ዳዊት በ70 ዓመት ዕድሜው ሞተ። ዳዊት ለ40 ዓመታት ገዝቷል፤ ከዚያ በኋላ ግን ሰሎሞን የእስራኤል ንጉሥ ሆነ