በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 63

ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን

ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን

ሰሎሞን ሲነግሥ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት ነበር። ይሖዋን ይወድ ነበር፤ አባቱ ዳዊት የሰጠውን ጥሩ ምክርም ተከትሏል። ይሖዋ በሰሎሞን ስለ ተደሰተ አንድ ቀን ሌሊት በሕልም ‘ሰሎሞን ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?’ አለው።

ሰሎሞን እንዲህ ሲል መለሰ:- ‘አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ እኔ ገና ወጣት ነኝ፤ ማስተዳደር የሚቻልበትንም መንገድ አላውቅም። ስለዚህ ሕዝብህን በትክክለኛው መንገድ ማስተዳደር የምችልበት ጥበብ ስጠኝ።’

ሰሎሞን የጠየቀው ነገር ይሖዋን አስደሰተው። ስለዚህ እንዲህ አለው:- ‘ረጅም ዕድሜን ወይም ሀብትን ሳይሆን ጥበብን ስለጠየቅህ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የበለጠ ጥበብ እሰጥሃለሁ። አንተ ያልጠየቅኸውን ሀብትና ክብርም እሰጥሃለሁ።’

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሁለት ሴቶች አንድ ከባድ ችግር ይዘው ሰሎሞን ፊት ቀረቡ። ከሴቶቹ መካከል አንዷ እንዲህ ስትል ገለጸች:- ‘ይቺ ሴትና እኔ የምንኖረው በአንድ ቤት ውስጥ ነው። እኔ አንድ ወንድ ልጅ ወለድኩ፤ ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ እሷም ወንድ ልጅ ወለደች። ከዚያም አንድ ቀን ሌሊት እሷ የወለደችው ልጅ ሞተ። ሆኖም እኔ ተኝቼ ሳለሁ የሞተውን ልጅዋን እኔ አጠገብ አስቀመጠችና የእኔን ልጅ ወሰደች። ከእንቅልፌ ነቅቼ የሞተውን ልጅ ስመለከት የእኔ ልጅ እንዳልሆነ አወቅኩ።’

በዚህ ጊዜ ሌላኛዋ ሴት ‘አይደለም! በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፤ የሞተው ደግሞ የእርሷ ነው!’ አለች። የመጀመሪያዋ ሴት መልሳ ‘አይደለም! የሞተው ልጅ የአንቺ ነው፤ በሕይወት ያለው ልጅ ደግሞ የእኔ ነው!’ አለች። ሴቶቹ እንዲህ እያሉ ይከራከሩ ነበር። ሰሎሞን ምን ያደርግ ይሆን?

ሰይፍ እንዲያመጡ አዘዘና ሰይፉን ሲያመጡ ‘በሕይወት ያለውን ልጅ ለሁለት ከፍላችሁ ለሁለቱም ግማሽ ግማሽ ስጧቸው’ አለ።

እውነተኛዋ እናት ‘አይሆንም!’ ብላ ጮኸች። ‘እባካችሁ ሕፃኑን አትግደሉት። ለእርሷ ስጧት!’ አለች። ሌላዋ ሴት ግን ‘ለሁለታችንም አትስጡን፤ ለሁለት ክፈሉት’ አለች።

በመጨረሻ ሰሎሞን ‘ልጁን አትግደሉት! ለመጀመሪያዋ ሴት ስጧት። እውነተኛዋ እናት እሷ ነች’ አለ። ሰሎሞን ይህን ሊያውቅ የቻለው እውነተኛዋ እናት ልጁን በጣም ስለምትወደው እንዳይገደል ስትል ለሌላኛዋ ሴት እንዲሰጥ ፈቃደኛ በመሆንዋ ነው። ሰሎሞን ይህን ችግር እንዴት እንደፈታው ሕዝቡ ሲሰሙ እንዲህ ያለ ጥበበኛ ንጉሥ በማግኘታቸው በጣም ተደሰቱ።

በሰሎሞን የግዛት ዘመን መሬቱ የተትረፈረፈ ስንዴ፣ ገብስ፣ ወይን፣ በለስና ሌሎችንም ምግቦች እንዲያበቅል በማድረግ አምላክ ሕዝቡን ባርኮታል። ሕዝቡ ጥሩ ጥሩ ልብሶችን ይለብሱ ነበር፤ እንዲሁም በሚያማምሩ ቤቶች ውስጥ ይኖሩ ነበር። ሁሉም ሰው ማንኛውንም ጥሩ ነገር እንደልቡ ማግኘት ይችል ነበር።