በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 67

ኢዮሣፍጥ በይሖዋ ተማመነ

ኢዮሣፍጥ በይሖዋ ተማመነ

እነዚህ ሰዎች እነማን እንደሆኑና ምን እያደረጉ እንዳሉ ታውቃለህ? ወደ ጦርነት እየሄዱ ነው፤ ከፊታቸው ያሉት ሰዎች ደግሞ እየዘመሩ ነው። ይሁን እንጂ ‘እየዘመሩ ያሉት ሰዎች የሚዋጉበት ሰይፍና ጦር ያልያዙት ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ኢዮሣፍጥ ሁለቱን ነገዶች ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ንጉሥ ነው። ኢዮሣፍጥ ይኖር የነበረው አሥሩን ነገዶች የያዘውን ሰሜናዊ መንግሥት ያስተዳድሩ የነበሩት ንጉሥ አክዓብና ኤልዛቤል በኖሩበት ዘመን ነው። ይሁን እንጂ ኢዮሣፍጥ ጥሩ ንጉሥ ነበር፤ አባቱ አሳም ጥሩ ንጉሥ ነበር። ስለዚህ ሁለቱን ነገዶች ባቀፈው የደቡብ መንግሥት ሥር የነበሩት ሰዎች ለብዙ ዓመታት ጥሩ ኑሮ ይኖሩ ነበር።

ይሁን እንጂ አሁን ሕዝቡን ፍርሃት ላይ የጣለ አንድ ነገር ተከስቷል። መልእክተኞች ወደ ኢዮሣፍጥ መጥተው ‘ከሞዓብ፣ ከአሞንና ከሴይር ተራራ አገሮች የተውጣጣ አንድ ትልቅ ሠራዊት አንተን ለመውጋት እየገሰገሰ ነው’ አሉት። ብዙ እስራኤላውያን የይሖዋን እርዳታ ለመጠየቅ ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዱ፤ በቤተ መቅደሱም ኢዮሣፍጥ ‘አምላካችን ይሖዋ ሆይ፣ ምን እንደምናደርግ አናውቅም። ይህን ትልቅ ሠራዊት መቋቋም አንችልም። እንድትረዳን እንማጸንሃለን’ ሲል ጸለየ።

ይሖዋ ጸሎቱን ሰማና ከአገልጋዮቹ መካከል አንዱ ሕዝቡን እንዲህ ሲል እንዲነግራቸው አደረገ:- ‘ውጊያው የእናንተ ሳይሆን የአምላክ ነው። እናንተ መዋጋት አያስፈልጋችሁም። ዝም ብላችሁ ቁሙና ይሖዋ እንዴት እንደሚያድናችሁ ተመልከቱ።’

ስለዚህ በነጋታው ጠዋት ኢዮሣፍጥ ሕዝቡን ‘በይሖዋ ተማመኑ!’ አላቸው። ከዚያም ከወታደሮቹ ፊት መዘምራኑ እንዲሄዱ አደረገ፤ በሚጓዙበት ጊዜም ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ይዘምሩ ነበር። ወደ ውጊያው ቦታ እየቀረቡ ሲሄዱ ምን እንደተፈጸመ ታውቃለህ? ይሖዋ የጠላት ወታደሮች እርስ በርሳቸው እንዲፋጁ አደረጋቸው። እስራኤላውያን ወደ ቦታው ሲደርሱ የጠላት ወታደር በሙሉ ሞቶ ነበር!

ኢዮሣፍጥ በይሖዋ መታመኑ ጥበብ አልነበረምን? እኛም በይሖዋ መታመናችን ጥበብ ነው።