በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 68

ከሞቱ በኋላ እንደገና ሕያው የሆኑ ሁለት ልጆች

ከሞቱ በኋላ እንደገና ሕያው የሆኑ ሁለት ልጆች

ሞተህ ቢሆን ኖሮና እንደገና ሕያው ብትሆን እናትህ ምን ይሰማት ነበር? በጣም ትደሰት ነበር! ይሁን እንጂ የሞተ ሰው እንደገና ሕያው መሆን ይችላል? ይህ ከዚህ በፊት ተፈጽሞ ያውቃል?

ሥዕሉ ላይ ያለውን ሰው፣ ሴትዮዋንና ትንሹን ልጅ ተመልከት። ሰውየው ነቢዩ ኤልያስ ነው። ሴትዮዋ በሰራፕታ ከተማ የምትኖር ባሏ የሞተባት ሴት ናት፤ ልጁ ደግሞ የእሷ ልጅ ነው። ከዕለታት አንድ ቀን ልጁ ታመመ። በሽታው ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት ሄደና በመጨረሻ ሞተ። በዚህ ጊዜ ኤልያስ ሴትዮዋን ‘ልጁን ስጪኝ’ አላት።

ኤልያስ የሞተውን ልጅ ወደ ላይኛው ክፍል ይዞት ሄደና አልጋ ላይ አስተኛው። ከዚያም ‘ይሖዋ ሆይ፣ ልጁን እንደገና ሕያው አድርገው’ ብሎ ጸለየ። ልጁ መተንፈስ ጀመረ! በዚህ ጊዜ ኤልያስ ልጁን ይዞ ወደ ታችኛው ክፍል ወረደና ሴትዮዋን ‘ተመልከቺ፣ ልጅሽ ሕያው ሆኗል!’ አላት። እናትየዋ በጣም የተደሰተችው ለዚህ ነው።

ሌላው የይሖዋ ታላቅ ነቢይ ኤልሳዕ ይባላል። የኤልያስ ረዳት ሆኖ ያገለግል ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ይሖዋ ኤልሳዕንም ተአምራት ለመፈጸም ተጠቅሞበታል። ከዕለታት አንድ ቀን ኤልሳዕ ሱነም ወደምትባል ከተማ ሄደ። በዚህች ከተማ የምትኖር አንዲት ሴት ብዙ መልካም ነገሮች አደረገችለት። ከጊዜ በኋላ ይቺ ሴት አንድ ወንድ ልጅ ወለደች።

ልጁ ካደገ በኋላ ከዕለታት አንድ ቀን ጠዋት በእርሻ ላይ እየሠራ ወደነበረው አባቱ ጋር ሄደ። ድንገት ልጁ ‘ራሴን አመመኝ!’ ብሎ ጮኸ። ልጁ እቤት ከወሰዱት በኋላ ሞተ። እናቱ ምንኛ አዝና ይሆን! ወዲያውኑ ሄደችና ኤልሳዕን ጠራችው።

ኤልሳዕ ወደ ሴትዮዋ ቤት ሲደርስ የሞተው ልጅ ወዳለበት ክፍል ገባ። ወደ ይሖዋ ጸለየና በልጁ ሰውነት ላይ ተኛ። ብዙም ሳይቆይ የልጁ ሰውነት ሞቀ፤ ከዚያም ሰባት ጊዜ አስነጠሰ። እናትየዋ ወደ ውስጥ ገብታ ልጅዋን ሕያው ሆኖ ስታገኘው ምንኛ ተደስታ ይሆን!

በጣም ብዙ ሰዎች ሞተዋል። ይህም ቤተሰቦቻቸውንና ጓደኞቻቸውን በጣም እንዲያዝኑ አድርጓቸዋል። እኛ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል የለንም። ይሖዋ ግን አለው። በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዴት ወደ ሕይወት እንደሚመልሳቸው ቆየት ብለን እንማራለን።