በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 73

የመጨረሻው የእስራኤል ጥሩ ንጉሥ

የመጨረሻው የእስራኤል ጥሩ ንጉሥ

ኢዮስያስ በደቡብ በሚገኙት በሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ሲነግሥ ገና ስምንት ዓመቱ ነበር። ይህ ዕድሜ ንጉሥ ለመሆን የሚያስችል አልነበረም። ስለዚህ ሕዝቡን ለማስተዳደር እንዲችል አንዳንድ ትልልቅ ሰዎች ይረዱት ነበር።

ኢዮስያስ ለሰባት ዓመት ከነገሠ በኋላ ይሖዋን መፈለግ ጀመረ። እንደ ዳዊት፣ ኢዮሣፍጥና ሕዝቅያስ ያሉትን ጥሩ ነገሥታት ምሳሌ ተከተለ። ከዚያም ኢዮስያስ ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለ አንድ ድፍረት የሚጠይቅ ሥራ አከናወነ።

አብዛኞቹ እስራኤላውያን ለረጅም ጊዜ በጣም መጥፎ ድርጊት ሲፈጽሙ ቆይተዋል። የሐሰት አማልክትን ያመልኩ ነበር። ለጣዖታት ይሰግዱ ነበር። ስለዚህ ኢዮስያስ ያገለግሉት ከነበሩት ሰዎች ጋር ሆኖ የሐሰት አምልኮን ከምድሪቱ ማጥፋት ጀመረ። በጣም ብዙ ሰዎች የሐሰት አማልክትን ያመልኩ ስለነበር ይህ ትልቅ ሥራ ነበር። ኢዮስያስና ያገለግሉት የነበሩት ሰዎች ጣዖታቱን ሲሰባብሩ ሥዕሉ ላይ ማየት ትችላለህ።

ከዚያ በኋላ ኢዮስያስ የይሖዋን ቤተ መቅደስ የመጠገኑን ሥራ እንዲያካሂዱ ሦስት ሰዎችን ሾመ። ከሕዝቡ ገንዘብ ከተሰበሰበ በኋላ ሥራውን ለማከናወን እንዲጠቀሙበት ለእነዚህ ሰዎች ተሰጠ። ቤተ መቅደሱን እያደሱ እያሉ ሊቀ ካህኑ ኬልቅያስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር አገኘ። ኬልቅያስ ያገኘው ነገር ከረጅም ጊዜ በፊት ይሖዋ ሙሴን ያስጻፈው የሕጉ መጽሐፍ ነበር። ለብዙ ዓመታት ጠፍቶ ነበር።

መጽሐፉን ወደ ኢዮስያስ ከወሰዱት በኋላ ኢዮስያስ መጽሐፉ እንዲነበብለት አደረገ። ኢዮስያስ የሕጉን ቃል ሲሰማ ሕዝቡ የይሖዋን ሕግ እንዳልጠበቁ አስተዋለ። በዚህ በጣም ስላዘነ ሥዕሉ ላይ እንደምታየው ልብሱን ቀደደ። ‘አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ ላይ የተጻፉትን ሕግጋት ባለመጠበቃቸው ይሖዋ በእኛ ላይ ተቆጥቷል’ አለ።

ይሖዋ ምን እርምጃ እንደሚወስድባቸው እንዲያጣራ ኢዮስያስ ሊቀ ካህናቱን ኬልቅያስን አዘዘው። ኬልቅያስ ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዶ ጠየቃት። ሕልዳናም ከይሖዋ የመጣውን የሚከተለውን መልእክት ተመልሶ ለኢዮስያስ እንዲያደርስ ነገረችው:- ‘ሕዝቡ የሐሰት አማልክት በማምለካቸውና ምድሪቱ በክፋት በመሞላቷ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡ በሙሉ ቅጣት ይደርስባቸዋል። ይሁን እንጂ አንተ መልካም ነገር ስላደረግህ ይህ ቅጣት የሚፈጸመው ከአንተ ሞት በኋላ ይሆናል።’