በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 75

በባቢሎን የነበሩ አራት ልጆች

በባቢሎን የነበሩ አራት ልጆች

ንጉሥ ናቡከደነፆር በደንብ የተማሩትን እስራኤላውያን በሙሉ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። ከዚያ በኋላ ንጉሡ ከወሰዳቸው እስራኤላውያን መካከል በጣም ቆንጆ የሆኑትንና ፈጣን የማስተዋል ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች መረጠ። ከእነዚህ መካከል አራቱ ሥዕሉ ላይ የምታያቸው ልጆች ናቸው። አንዱ ዳንኤል ሲሆን ሌሎቹ ሦስቱ ደግሞ ባቢሎናውያን ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ብለው ስም ያወጡላቸው ልጆች ናቸው።

ናቡከደነፆር ወጣቶቹ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ እንዲያገለግሉ ሊያሰለጥናቸው አቀደ። ለሦስት ዓመት እንዲሰለጥኑ ካደረገ በኋላ ችግሮችን ለመፍታት እንዲረዱት የተሻለ የማስተዋል ችሎታ ያላቸውን ብቻ ለመምረጥ አሰበ። ንጉሡ ልጆቹ በሚሠለጥኑበት ጊዜ ጠንካራና ጤናማ እንዲሆኑ ፈልጎ ነበር። ስለዚህ አገልጋዮቹ እሱና ቤተሰቡ የሚመገቡትን ብዙ ዓይነት ምግብና ወይን ለሁሉም እንዲሰጧቸው አዘዛቸው።

ወጣቱን ዳንኤልን ተመልከተው። የናቡከደነፆር ዋና አገልጋይ የሆነውን አስፋኔዝን ምን እያለው እንዳለ ታውቃለህ? በንጉሡ ማዕድ የሚቀርቡትን ብዙ ዓይነት ምግቦች መመገብ እንደማይፈልግ እየነገረው ነው። አስፋኔዝ ግን ተጨንቋል። ‘ንጉሡ ምን መብላት እንዳለባችሁና ምን መጠጣት እንዳለባችሁ ወስኗል። እንደሌሎቹ ወጣቶች ጤናማ ሆናችሁ ካልተገኛችሁ ንጉሡ ሊገድለኝ ይችላል’ አለ።

ዳንኤል ለእሱና ለሦስቱ ጓደኞቹ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያደርግላቸው አስፋኔዝ ወደሾመው ሰው ሄደ። ‘እባክህ ለ10 ቀናት ፈትነን። ጥቂት የምንበላው አትክልትና የምንጠጣው ውኃ ስጠን። ከዚያም ንጉሡ የሚመገበውን ምግብ ከሚመገቡት ሌሎች ወጣቶች ጋር አስተያየንና ማን የተሻለ እንደሚሆን ተመልከት’ አለው።

ሰውየው በዚህ ተስማማ። አሥሩ ቀናት ሲያበቁ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ከሌሎቹ ሁሉ ይበልጥ ጤናሞች ሆነው ተገኙ። ስለዚህ አስፈላጊውን እንክብካቤ ያደርግላቸው የነበረው ሰው በንጉሡ ምግብ ፋንታ የአትክልት ምግቦችን መመገባቸውን እንዲቀጥሉ ፈቀደላቸው።

ሦስቱ ዓመታት ሲያበቁ ወጣቶቹ በሙሉ ናቡከደነፆር ፊት ቀረቡ። ንጉሡ ሁሉንም ካነጋገራቸው በኋላ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ የተሻለ የማስተዋል ችሎታ እንዳላቸው ተረዳ። ስለዚህ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ሆነው እንዲረዱት እዚያው አስቀራቸው። ዳንኤል፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ምንጊዜም ንጉሡ ጥያቄ ወይም ከባድ ችግር ሲያቀርብላቸው ከእሱ ካህናትና ጠቢባን 10 ጊዜ እጥፍ የተሻለ የመፍትሔ ሐሳብ ያቀርቡ ነበር።