በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 79

ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ

ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ

ኧረ! ዳንኤል አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ያለ ይመስላል። ነገር ግን አንበሶቹ ምንም አልነኩትም! ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? ዳንኤልን እነዚህ ሁሉ አንበሶች ወዳሉበት ወደዚህ ቦታ የጨመረው ማን ነው? እስቲ እንመልከት።

በዚህ ወቅት የባቢሎን ንጉሥ የነበረው ዳርዮስ የተባለ ሰው ነበር። ዳንኤል በጣም ደግና ጥበበኛ ስለነበረ ዳርዮስ በጣም ይወደው ነበር። ዳርዮስ ዳንኤልን በመንግሥቱ ውስጥ ዋና ገዥ አድርጎ ሾመው። ይህም በመንግሥቱ ውስጥ ሥልጣን የነበራቸው ሌሎች ሰዎች በዳንኤል ላይ ቅናት እንዲያድርባቸው አደረጋቸው፤ ስለዚህ የሚከተለውን ነገር አደረጉ።

ወደ ዳርዮስ ሄዱና እንዲህ አሉት:- ‘ንጉሥ ሆይ፣ ለ30 ቀናት ወደ አንተ ወደ ንጉሡ ካልሆነ በቀር ማንም ሰው ወደ ሌላ አምላክም ሆነ ሰው እንዳይጸልይ የሚያግድ ሕግ እንድታወጣ አስበናል። ይህን ሕግ የጣሰ ሰው ቢገኝ ወደ አንበሶች ጉድጓድ ይጣል።’ ዳርዮስ እነዚህ ሰዎች ይህ ሕግ እንዲወጣ የፈለጉበትን ምክንያት አላወቀም ነበር። ይሁን እንጂ ያቀረቡት ሐሳብ ጥሩ መስሎ ስለታየው ሕጉ እንዲጻፍ አደረገ። ከዚህ በኋላ ሕጉ ሊለወጥ አይችልም።

ዳንኤል የወጣውን ሕግ ሲሰማ ሁልጊዜ ያደርገው እንደነበረው ወደ ቤቱ ሄደና ጸለየ። ክፉዎቹ ሰዎች ዳንኤል ወደ ይሖዋ መጸለዩን እንደማያቆም ያውቁ ነበር። ዳንኤልን ለማጥፋት ያወጡት ዕቅድ የተሳካ መስሎ ስለታያቸው ተደሰቱ።

ንጉሥ ዳርዮስ እነዚህ ሰዎች ይህ ሕግ እንዲወጣ የፈለጉበትን ምክንያት ሲረዳ በጣም አዘነ። ይሁን እንጂ ሕጉን መለወጥ ስለማይችል ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ ማስተላለፍ ነበረበት። ቢሆንም ንጉሡ ዳንኤልን ‘የምታገለግለው አምላክህ እንደሚያድንህ ተስፋ አደርጋለሁ’ አለው።

ዳርዮስ በጣም አዝኖ ስለነበር በዚያ ሌሊት እንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት በፍጥነት ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ ሄደ። ሥዕሉ ላይ ልታየው ትችላለህ። ‘የሕያው አምላክ አገልጋይ የሆንከው ዳንኤል ሆይ፣ የምታገለግለው አምላክ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሏልን?’ ሲል ጮኸ።

ዳንኤል ‘አምላክ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ስለዘጋ ምንም አልነኩኝም’ ሲል መለሰለት።

ንጉሡ በጣም ተደሰተ። ዳንኤልን ከጉድጓዱ ውስጥ እንዲያወጡት አዘዘ። ከዚያም ዳንኤል ወደ አንበሶቹ ጉድጓድ ተጥሎ እንዲጠፋ ለማድረግ የሞከሩት መጥፎ ሰዎች ጉድጓዱ ውስጥ እንዲጣሉ አደረገ። ሰዎቹ ገና መሬት ሳይደርሱ አንበሶቹ ያዟቸውና ቆረጣጠሟቸው።

ከዚያም ንጉሥ ዳርዮስ በመንግሥቱ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ እንዲህ ሲል ጻፈ:- ‘ሁሉም ሰው የዳንኤልን አምላክ እንዲያከብር አዝዣለሁ። ታላላቅ ተአምራትን ያደርጋል። ዳንኤልን ከአንበሶች አፍ አድኖታል።’

ዳንኤል 6:​1-281980 ትርጉም