በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 80

የአምላክ ሕዝቦች ከባቢሎን ወጡ

የአምላክ ሕዝቦች ከባቢሎን ወጡ

ሜዶናውያንና ፋርሳውያን ባቢሎንን ከያዙ ወደ ሁለት ዓመት የሚጠጋ ጊዜ አልፎ ነበር። አሁን ምን እየተፈጸመ እንዳለ ተመልከት! አዎ፣ እስራኤላውያን ከባቢሎን እየወጡ ነው። ነፃ ሊወጡ የቻሉት እንዴት ነው? እንዲሄዱ የፈቀደላቸው ማን ነው?

የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ነው። ቂሮስ ከመወለዱ ከብዙ ጊዜ በፊት ይሖዋ ነቢዩ ኢሳይያስ እርሱን አስመልክቶ ‘እኔ እንድታደርግ የምፈልገውን ነገር ሁሉ ታደርጋለህ። ከተማይቱን መያዝ እንድትችል በሮችዋ ክፍት ይሆኑልሃል’ ብሎ እንዲጽፍ አድርጎ ነበር። ባቢሎንን ለመያዝ የዘመተውን ሠራዊት ይመራ የነበረው ቂሮስ ነው። ሜዶናውያንና ፋርሳውያን በሌሊት መጥተው ክፍት በነበሩት በሮች በኩል ወደ ከተማይቱ ገቡ።

ይሁን እንጂ የይሖዋ ነቢይ የሆነው ኢሳይያስ ቂሮስ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ እንደገና እንዲገነቡ ትእዛዝ እንደሚያወጣም ተናግሮ ነበር። ቂሮስ ይህን ትእዛዝ አውጥቷል? አዎ፣ አውጥቷል። ቂሮስ እስራኤላውያንን ‘ሂዱና ኢየሩሳሌምንና የአምላካችሁን የይሖዋን ቤተ መቅደስ ገንቡ’ አላቸው። እነዚህ እስራኤላውያን እዚያ እንደደረሱ የሚያከናውኑት ነገር ይህንኑ ነበር።

ይሁን እንጂ በባቢሎን የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ረጅሙን ጉዞ ተጉዘው ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ አይችሉም ነበር። ጉዞው ወደ 500 ማይልስ (800 ኪሎ ሜትር) የሚጠጋ በጣም ረጅም ጉዞ የነበረ ሲሆን ብዙዎቹ በጣም አርጅተው ወይም ታመው ስለነበረ ወደ ሩቅ ቦታ መጓዝ አይችሉም ነበር። አንዳንድ ሰዎች መሄድ የማይችሉባቸው ሌሎች ምክንያቶችም ነበሩ። ሆኖም ቂሮስ የማይሄዱትን ሰዎች ‘ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ለመገንባት ለሚመለሱት ሰዎች ብርና ወርቅ እንዲሁም ሌሎች ስጦታዎችን ስጧቸው’ ብሏቸው ነበር።

ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ ያሉት እነዚህ ሰዎች ብዙ ስጦታዎች ተሰጥቷቸው ነበር። በተጨማሪም ቂሮስ ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ሲያጠፋ ከይሖዋ ቤተ መቅደስ የወሰዳቸውን ጎድጓዳ ሳህኖችና ጽዋዎች ሰጥቷቸው ነበር። ሕዝቡ ይዘውት የሚመለሱት ብዙ ነገር ነበር።

እስራኤላውያን ከአራት ወራት ጉዞ በኋላ ልክ በተባለው ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ከተማይቱ ከጠፋች ልክ 70 ዓመት ሆኗት ነበር፤ በምድሪቱ ላይ የሚኖር አንድም ሰው አልነበረም። ይሁን እንጂ ቀጥሎ እንደምንመለከተው እስራኤላውያን ወደ ራሳቸው አገር የተመለሱ ቢሆኑም እንኳ አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸው ነበር።