በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 82

መርዶክዮስና አስቴር

መርዶክዮስና አስቴር

ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም ከመመለሱ በፊት ወደነበሩት ጥቂት ዓመታት እስቲ መለስ እንበል። መርዶክዮስና አስቴር በፋርስ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው እስራኤላውያን ነበሩ። አስቴር ንግሥት የነበረች ሲሆን የአጎቷ ልጅ መርዶክዮስ ደግሞ በሥልጣን ላይ ከነበረው ንጉሥ ቀጥሎ ያለውን ከፍተኛ ሥልጣን የያዘ ሰው ነበር። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ እስቲ እንመልከት።

አስቴር ወላጆቿ የሞቱት ገና ትንሽ ሳለች ስለነበረ ያሳደጋት መርዶክዮስ ነው። የፋርሱ ንጉሥ አሐሽዌሮሽ በሱሳ ከተማ ውስጥ አንድ ቤተ መንግሥት ነበረው፤ መርዶክዮስ ከእሱ አገልጋዮች አንዱ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን የንጉሡ ሚስት አስጢን ለእርሱ ባለመታዘዟ ንጉሡ ንግሥት የምትሆን አዲስ ሚስት መረጠ። ንጉሡ የመረጣት ሴት ማን እንደሆነች ታውቃለህ? አዎ፣ ወጣቷና ቆንጆዋ አስቴር ነበረች።

ሰዎቹ እየሰገዱለት ያሉትን ይህን ኩራተኛ ሰው አየኸው? ይህ ሰው ሐማ ይባላል። በፋርስ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ሰው ነው። ሐማ ይህ ቁጭ ብሎ የምትመለከተው መርዶክዮስ የተባለውም ሰው እንደ ሌሎቹ ሰዎች እንዲሰግድለት ይፈልግ ነበር። መርዶክዮስ ግን አልሰገደለትም። ለእንዲህ ዓይነት መጥፎ ሰው መስገድ ትክክል መስሎ አልታየውም። ይህም ሐማን በጣም አስቆጣው። ስለዚህ የሚከተለውን ነገር አደረገ።

ሐማ ለንጉሡ ስለ እስራኤላውያን የሐሰት ወሬ ነገረው። ‘ለሕጎችህ የማይታዘዙ መጥፎ ሰዎች ስለሆኑ መገደል አለባቸው’ አለው። አሐሽዌሮሽ ሚስቱ አስቴር እስራኤላዊት እንደሆነች አያውቅም ነበር። ስለዚህ ሐማን ሰምቶ እስራኤላውያን በሙሉ በአንድ የተወሰነ ቀን እንዲገደሉ አዘዘ።

መርዶክዮስ ይህን ትእዛዝ ሲሰማ በጣም አዘነ። ‘ንጉሡን አነጋግረሽ እንዲያድነን ለምኚው’ የሚል መልእክት ወደ አስቴር ላከ። በፋርስ ሕግ መሠረት አንድ ሰው ሳይጠራ ንጉሡን ሄዶ ማነጋገር አይችልም ነበር። ቢሆንም አስቴር ሳትጠራ ወደ ንጉሡ ሄደች። ንጉሡ የወርቅ በትሩን ዘረጋላት፤ ይህም አስቴር እንደማትገደል የሚያሳይ ነበር። አስቴር ንጉሡንና ሐማን ባዘጋጀችው ግብዣ ላይ እንዲገኙ ጠራቻቸው። በግብዣውም ላይ ንጉሡ አስቴር ምን እንዲያደርግላት እንደምትፈልግ ጠየቃት። አስቴር እሱና ሐማ በቀጣዩ ቀን በምታዘጋጀው ግብዣ ላይ ከተገኙ ከእሱ የምትፈልገውን ነገር እንደምትነግረው ገለጸችለት።

በዚያ ግብዣ ላይ አስቴር ንጉሡን ‘ሕዝቤና እኔ ልንገደል ነው’ አለችው። ንጉሡ ተቆጣ። ‘ይህን ለማድረግ የደፈረው ማን ነው?’ ሲል ጠየቃት።

አስቴር ‘ይህን ያደረገው ጠላታችን፣ ይህ ክፉ ሰው ሐማ ነው!’ ብላ መለሰችለት።

በዚህ ጊዜ ንጉሡ በጣም ተቆጣ። ሐማ እንዲገደል አዘዘ። ከዚያ በኋላ ንጉሡ ለመርዶክዮስ ከእሱ ቀጥሎ ያለውን ከፍተኛ ሥልጣን ሰጠው። ከዚያም መርዶክዮስ እስራኤላውያን ይገደላሉ በተባለበት ቀን ሕይወታቸውን ለማዳን መዋጋት የሚያስችላቸው አዲስ አዋጅ እንዲታወጅ አደረገ። በዚህ ወቅት መርዶክዮስ ይህን ከፍተኛ ሥልጣን ይዞ ስለነበረ እስራኤላውያንን ብዙ ሰዎች ረዷቸውና ከጠላቶቻቸው ዳኑ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የአስቴር መጽሐፍ