በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 83

የኢየሩሳሌም ግንብ

የኢየሩሳሌም ግንብ

እየተካሄደ ያለውን ሥራ ተመልከት። እስራኤላውያን የኢየሩሳሌምን ግንብ በመገንባቱ ሥራ ተጠምደዋል። ንጉሥ ናቡከደነፆር ከ152 ዓመታት በፊት ኢየሩሳሌምን ሲያጠፋ ግንቧን አፈራርሶ የከተማይቷን በሮች በእሳት አቃጥሎ ነበር። እስራኤላውያን ከባቢሎን ወደ አገራቸው በተመለሱበት ወቅት የኢየሩሳሌምን ግንቦች መልሰው አልገነቧቸውም ነበር።

ሕዝቡ በከተማይቱ ዙሪያ ምንም ግንብ ሳይኖር ይህን ሁሉ ዓመት በዚህ ቦታ ሲኖሩ ምን ይሰማቸው የነበረ ይመስልሃል? ስጋት ነበረባቸው። ጠላቶቻቸው በቀላሉ ወደ ከተማይቱ ገብተው ሊያጠቋቸው ይችሉ ነበር። አሁን ግን ነህምያ የተባለው ሰው ሕዝቡ ግንቡን መልሰው እንዲገነቡ እየረዳቸው ነው። ነህምያ ማን እንደሆነ ታውቃለህ?

ነህምያ መርዶክዮስና አስቴር ይኖሩበት ከነበረው ከሱሳ ከተማ የመጣ እስራኤላዊ ሰው ነው። ነህምያ በንጉሡ ቤተ መንግሥት ውስጥ ይሠራ ስለነበረ የመርዶክዮስና የንግሥት አስቴር ጥሩ ጓደኛ የነበረ ሰው ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ነህምያ የአስቴር ባል የነበረውን ንጉሥ አሐሽዌሮሽን ያገለግል ነበር አይልም። ነህምያ ያገለግል የነበረው ቀጥሎ የነገሠውን ንጉሥ አርጤክስስን ነበር።

አርጤክስስ የይሖዋን ቤተ መቅደስ ለማስዋብ የተጠቀሙበትን ያን ሁሉ ገንዘብ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲወስድ ለዕዝራ የሰጠው ጥሩው ንጉሥ እንደሆነ አስታውስ። ይሁን እንጂ ዕዝራ የፈረሰውን የከተማይቱን ግንብ አልገነባውም። ነህምያ ይህን ሥራ ሊሠራ የቻለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

አርጤክስስ ቤተ መቅደሱን ለማስዋብ የሚያገለግለውን ገንዘብ ለዕዝራ ከሰጠው 13 ዓመት አልፎ ነበር። በዚህ ወቅት ነህምያ የንጉሥ አርጤክስስ ዋነኛ ወይን ጠጅ አሳላፊ ነበር። ለንጉሡ ወይን ጠጅ የማቅረብና ማንም ሰው መርዝ ቀላቅሎ ንጉሡን ለመግደል እንዳይሞክር የመከታተል ኃላፊነት ነበረበት ማለት ነው። ይህ ትልቅ ሥራ ነበር።

ከዕለታት አንድ ቀን የነህምያ ወንድም የሆነው አናኒና ሌሎች ሰዎች ነህምያን ለመጠየቅ ከእስራኤል አገር ተነስተው መጡ። እስራኤላውያን ያለባቸውን ችግርና የፈራረሰው የኢየሩሳሌም ግንብ አሁንም ድረስ እንዳልተገነባ ነገሩት። ነህምያ በዚህ በጣም በማዘን ወደ ይሖዋ ጸለየ።

አንድ ቀን ንጉሡ ነህምያ ማዘኑን አስተውሎ ‘ያዘንከው ለምንድን ነው?’ ሲል ጠየቀው። ነህምያ ያዘነው ኢየሩሳሌም መጥፎ ሁኔታ ላይ የምትገኝ በመሆኑና ግንቧም በመፈራረሱ እንደሆነ ገለጸለት። ‘ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?’ ሲል ንጉሡ ጠየቀው።

ነህምያ ‘ወደ ኢየሩሳሌም ሄጄ ግንቡን መልሼ እንድገነባ ፍቀድልኝ’ ሲል መለሰለት። ንጉሥ አርጤክስስ ደግ ነበር። ነህምያን መሄድ እንደሚችል ነገረው፤ የተወሰነውን የግንባታ ሥራ ለማካሄድ የሚያገለግል እንጨት ማግኘት እንዲችልም ረዳው። ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ከመጣ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ዕቅዱን ለሕዝቡ ነገራቸው። ሕዝቡ በሐሳቡ በመስማማት ‘መሥራት እንጀምር’ አሉ።

የእስራኤላውያን ጠላቶች ግንቡ እየተሠራ መሆኑን ሲመለከቱ ‘ሄደን እንገድላቸውና ግንባታውን እንዲያቆሙ እናደርጋቸዋለን’ አሉ። ይሁን እንጂ ነህምያ ይህን ሰማና ለሠራተኞቹ ሰይፍና ጦር ሰጣቸው። ‘ጠላቶቻችንን አትፍሯቸው። ወንድሞቻችሁን፣ ልጆቻችሁን፣ ሚስቶቻችሁንና ቤቶቻችሁን ለማዳን ተዋጉ’ አላቸው።

ሕዝቡ በጣም ደፋሮች ነበሩ። የጦር መሣሪያዎቻቸውን ቀን ከሌት ታጥቀው መሥራታቸውን ቀጠሉ። ግንቡ በ52 ቀናት ውስጥ ተሠርቶ አለቀ። ከዚህ በኋላ በከተማይቱ ውስጥ ያሉት ሰዎች ስጋት አያድርባቸውም። ነህምያና ዕዝራ ሕዝቡን የአምላክን ሕግ አስተማሯቸው፤ ሕዝቡም ተደሰቱ።

ይሁን እንጂ በዚህም ወቅት ሁኔታው እስራኤላውያን ወደ ባቢሎን እስረኞች ሆነው ከመወሰዳቸው በፊት የነበረውን ዓይነት አልነበረም። ሕዝቡ በፋርስ ንጉሥ ይገዙ ነበር፤ እርሱን የማገልገል ግዴታ ነበረባቸው። ሆኖም ይሖዋ አዲስ ንጉሥ እንደሚልክላቸውና ይህ ንጉሥ ለሕዝቡ ሰላምን እንደሚያመጣ ቃል ገብቶላቸው ነበር። ይህ ንጉሥ ማን ነው? ለምድር ሰላምን የሚያመጣው እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙ 450 የሚያህሉ ዓመታት አለፉ። ከዚያም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አንድ ሕፃን ተወለደ። ይሁን እንጂ ይህ ራሱን የቻለ ታሪክ ነው።