በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 84

አንድ መልአክ ማርያምን አነጋገራት

አንድ መልአክ ማርያምን አነጋገራት

ይቺ ቆንጆ ሴት ማርያም ነች። በናዝሬት ከተማ ውስጥ የምትኖር አንዲት እስራኤላዊት ናት። አምላክ ማርያም በጣም ጥሩ ሴት እንደሆነች ያውቅ ነበር። ገብርኤል የተባለውን መልአኩን እንዲያነጋግራት ወደ እርሷ የላከውም ለዚህ ነበር። ገብርኤል ለማርያም ምን ሊነግራት እንደመጣ ታውቃለህ? እስቲ እንመልከት።

ገብርኤል ‘አንቺ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ሰላም ላንቺ ይሁን። ይሖዋ ከአንቺ ጋር ነው’ አላት። ማርያም ይህን ሰው ከዚህ በፊት አይታው አታውቅም ነበር። ምን ማለቱ እንደሆነ ስላልገባት ተጨነቀች። ይሁን እንጂ ገብርኤል ወዲያውኑ አረጋጋት።

‘ማርያም ሆይ፣ አትፍሪ። በይሖዋ ፊት ሞገስ አግኝተሻል። በዚህም ምክንያት አንድ ልዩ ነገር ያደርግልሻል። በቅርቡ ልጅ ትወልጃለሽ። ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ’ አላት።

ገብርኤል ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ:- ‘ይህ ልጅ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል አምላክ ልጅም ይባላል። ይሖዋ ልክ እንደ ዳዊት ንጉሥ ያደርገዋል። ሆኖም ኢየሱስ የዘላለም ንጉሥ ይሆናል፤ መንግሥቱም ፍጻሜ አይኖረውም!’

ማርያም ‘ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? እኔ ገና አላገባሁም። ከወንድ ጋር ሳልተኛ እንዴት ልጅ ልወልድ እችላለሁ?’ ስትል ጠየቀችው።

‘የአምላክ ኃይል በአንቺ ላይ ይመጣል። ስለዚህ ልጁ የአምላክ ልጅ ይባላል’ በማለት ገብርኤል መለሰላት። ከዚያም ማርያምን እንዲህ አላት:- ‘ዘመድሽን ኤልሳቤጥን አስታውሺ። ሰዎች ስላረጀች ልጅ መውለድ አትችልም ብለው ነበር። ሆኖም በቅርቡ ልጅ ትወልዳለች። አምላክ የሚሳነው ነገር የለም።’

ወዲያውኑ ማርያም ‘እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ። እንደ ቃልህ ይሁንልኝ’ አለችው። ከዚያም መልአኩ ሄደ።

ማርያም በፍጥነት ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ሄደች። ኤልሳቤጥ የማርያምን ድምፅ ስትሰማ በማኅፀኗ ውስጥ ያለው ሕፃን በደስታ ዘለለ። ኤልሳቤጥ በአምላክ መንፈስ ተሞልታ ማርያምን ‘አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ’ አለቻት። ማርያም ኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወር ያህል ከተቀመጠች በኋላ ናዝሬት ወደሚገኘው ቤቷ ተመለሰች።

ዮሴፍ የተባለ አንድ ሰው ማርያምን ሊያገባ አስቦ ነበር። ሆኖም ዮሴፍ ማርያም ማርገዟን ሲያውቅ ሊተዋት ፈለገ። በዚህ ጊዜ የአምላክ መልአክ ‘ማርያምን ሚስት አድርገህ ለመውሰድ አትፍራ። ልጅ የሰጣት አምላክ ነው’ አለው። ስለዚህ ማርያምና ዮሴፍ ተጋቡና ኢየሱስ የሚወለድበትን ጊዜ መጠባበቅ ጀመሩ።