በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 86

በኮከብ እየተመሩ የመጡ ሰዎች

በኮከብ እየተመሩ የመጡ ሰዎች

ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ በእጁ እየጠቆመ ያለውን ደማቅ ኮከብ አየኸው? ኢየሩሳሌምን ለቀው ሲወጡ ኮከቡ ብቅ አለ። እነዚህ ሰዎች ከምሥራቅ የመጡ ሲሆኑ ከዋክብትን የሚያጠኑ ሰዎች ናቸው። ይህ አዲስ ኮከብ ወደ አንድ ታላቅ ሰው እየመራን ነው የሚል እምነት ነበራቸው።

ሰዎቹ መጀመሪያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ ‘የአይሁድ ንጉሥ የሚሆነው ልጅ ያለው የት ነው?’ ሲሉ ጠየቁ። “አይሁድ” እስራኤላውያን የሚጠሩበት ሌላ ስም ነው። ሰዎቹ ‘የልጁን ኮከብ በምሥራቅ ሳለን አይተን ልንሰግድለት መጥተናል’ አሉ።

የኢየሩሳሌም ንጉሥ የነበረው ሄሮድስ ይህን ሲሰማ ተበሳጨ። ሥልጣኑን ሌላ ንጉሥ እንዲወስድበት አይፈልግም ነበር። ስለዚህ ሄሮድስ የካህናት አለቆችን ጠርቶ ‘ቃል የተገባለት ንጉሥ የሚወለደው የት ነው?’ ሲል ጠየቃቸው። ‘መጽሐፍ ቅዱስ በቤተ ልሔም እንደሚወለድ ይናገራል’ ብለው መለሱለት።

ስለዚህ ሄሮድስ ከምሥራቅ የመጡትን ሰዎች ጠርቶ ‘ሂዱና ሕፃኑን ፈልጉ። ስታገኙት ንገሩኝ። እኔም ሄጄ ልሰግድለት እፈልጋለሁ’ አላቸው። ይሁን እንጂ ሄሮድስ ልጁን ለማግኘት የፈለገው እርሱን ለመግደል አስቦ ነው!

ከዚያም ኮከቡ ከሰዎቹ ፊት እየሄደ ወደ ቤተ ልሔም መራቸውና ልጁ ያለበት ቦታ ጋር ሲደርስ ቆመ። ሰዎቹ ቤቱ ውስጥ ሲገቡ ማርያምንና ሕፃኑን ኢየሱስ አገኟቸው። ስጦታዎችን አወጡና ለኢየሱስ ሰጡት። በኋላ ግን ይሖዋ ሰዎቹ ሄሮድስ ጋር ተመልሰው እንዳይሄዱ በሕልም አስጠነቀቃቸው። ስለዚህ ሰዎቹ በሌላ መንገድ አድርገው ወደ ራሳቸው አገር ተመለሱ።

ሄሮድስ ከምሥራቅ የመጡት ሰዎች ወደ አገራቸው እንደተመለሱ ሲሰማ በጣም ተቆጣ። በዚህም ምክንያት በቤተ ልሔም ያሉ ሁለት ዓመት የሞላቸውና ከዚያ ያነሰ ዕድሜ ያላቸው ወንዶች ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ አዘዘ። ይሁን እንጂ ይሖዋ አስቀድሞ በሕልም ዮሴፍን አስጠንቅቆት ስለነበረ ዮሴፍ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ግብጽ ሄደ። ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ሄሮድስ እንደሞተ ሲሰማ ማርያምንና ኢየሱስን ይዞ ወደ አገሩ ወደ ናዝሬት ተመለሰ። ኢየሱስ ያደገው በዚህ ቦታ ነበር።

ይህ አዲስ ኮከብ እንዲወጣ ያደረገው ማን ይመስልሃል? ሰዎቹ ኮከቡን ካዩ በኋላ መጀመሪያ የሄዱት ወደ ኢየሩሳሌም እንደሆነ አስታውስ። ሰይጣን ዲያብሎስ የአምላክን ልጅ ለመግደል ይፈልግ ነበር፤ የኢየሩሳሌሙ ንጉሥ ሄሮድስም እሱን ለመግደል እንደሚጥር ያውቅ ነበር። ስለዚህ ይህ ኮከብ እንዲወጣ ያደረገው ሰይጣን መሆን አለበት።