በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 87

ወጣቱ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ውስጥ

ወጣቱ ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ውስጥ

ከእነዚህ ትልልቅ ሰዎች ጋር እየተነጋገረ ያለውን ልጅ ተመልከት። ሰዎቹ ኢየሩሳሌም በሚገኘው የአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበሩ አስተማሪዎች ናቸው። ልጁ ደግሞ ኢየሱስ ነው። አሁን አድጎ የ12 ዓመት ልጅ ሆኗል።

ኢየሱስ ስለ አምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተጻፉት ነገሮች ብዙ የሚያውቅ መሆኑ አስተማሪዎቹን በጣም አስደነቃቸው። ይሁን እንጂ ዮሴፍና ማርያም እዚህ የሌሉት ለምንድን ነው? የት ናቸው? እስቲ እንመርምር።

ዮሴፍ በየዓመቱ የማለፍ በዓል የሚባለውን ልዩ በዓል ለማክበር ቤተሰቡን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣ ነበር። ከናዝሬት እስከ ኢየሩሳሌም ያለው መንገድ ረጅም ነው። ማንም ሰው መኪና አልነበረውም፤ ባቡሮችም አልነበሩም። በዚያ ዘመን ሰዎች እነዚህ ነገሮች የሏቸውም ነበር። አብዛኞቹ ሰዎች የሚጓዙት በእግራቸው ሲሆን ኢየሩሳሌም ለመድረስም ወደ ሦስት ቀን ገደማ ይወስድባቸዋል።

በዚህ ወቅት ዮሴፍ ትልቅ ቤተሰብ ነበረው። ስለዚህ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ሌሎች የኢየሱስ ታናናሽ ወንድሞችና እህቶች ነበሩ። በዚህ ዓመት ዮሴፍና ማርያም ወደ ናዝሬት ለመመለስ ልጆቻቸውን ይዘው ረጅሙን ጉዞ ተያያዙት። ኢየሱስ ከሌሎች መንገደኞች ጋር እየመጣ እንዳለ አድርገው አስበው ነበር። ሆኖም ቀኑ መሽቶ ከጉዟቸው ሲያርፉ ኢየሱስን ሊያገኙት አልቻሉም። ከዘመዶቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር እንዳለ ብለው ቢፈልጉትም ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም! ስለዚህ እሱን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

በመጨረሻ በዚህ ቦታ ከአስተማሪዎቹ ጋር ሲነጋገር አገኙት። እያዳመጣቸውና ጥያቄዎች እየጠየቃቸው ነበር። ሰዎቹ ሁሉ በኢየሱስ ጥበብ ተደንቀው ነበር። ሆኖም ማርያም ‘ልጄ ሆይ፣ እንዲህ ያደረግህብን ለምንድን ነው? አባትህና እኔ በጣም ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር’ አለችው።

ኢየሱስ ‘ለምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት መሆን እንዳለብኝ አታውቁምን?’ ሲል መለሰላት።

አዎ፣ ኢየሱስ ስለ አምላክ መማር በሚችልበት ቦታ መሆን ይፈልግ ነበር። እኛም እንዲህ ሊሰማን አይገባምን? ኢየሱስ ናዝሬት በነበረበት ወቅት በየሳምንቱ ለአምልኮ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ ነበር። ዘወትር እነዚህን ስብሰባዎች በሚገባ ይከታተል ስለነበረ ከመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ነገሮችን ተምሮ ነበር። የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል እርሱን እንምሰል።